ሻምበል ጉታ ዲንቃ፡ የነጻነት ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን ከሞት ያተረፉት ኢትዮጵያዊ

ይህ የተከሰተው የዛሬ 60 ዓመት ነው። ወቅቱ በርካታ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የነበሩበትና ነጻነታቸውንም ለማግኘት መራር ትግል የሚያካሄዱበት ጊዜ ነበር።

ኢትዮጵያ ደግሞ በአድዋ ጦርነት ጣልያንን ድል አድርጋ፣ ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ ይችላሉ በሚል ብዙ የአፍሪካ አገራት ምሳሌያቸው አድርገው ወስደዋታል።

በደቡብ አፍሪካም የቅኝ ግዛትን ተቃውመው ትግል ከጀመሩት መካከል አንዱ የሆነው የፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴ ይጠቀሳል።

በዚህ ውስጥ ደግሞ የኔልሰን ማንዴላ ድርሻ ትልቅ ነው።

በ1954 ዓ.ም. ማንዴላ ስማቸውን ዴቪት ማትሶማይ በሚል ፓስፖርት ተዘጋጅቶላቸው፣ ሥራቸው ጋዜጠኛ በሚል ተጠቅሶ ወደ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ መጡ።

ሥልጠናውን ከመውሰዳቸው በፊት ግን ኢትዮጵያ አሠልጣኝ እና ጠባቂ ለመመደብ ሽር ጉድ ብላለች።

በዚህ መካከል ነው የወቅቱ ሻምበል ጉቱ ዲንቃን ታሪክ የሚያነሳቸው።

ጉታ ዲንቃ ደብሱ በ1928 በምዕራብ ሸዋ ቶኬ ሌንጫ ጊዮርጊስ ከሚባል አካባቢ ነው የተወለዱት።

ከ20 ዓመት በኋላ በ1948 ዓ.ም በጉደር ከተማ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከስድስተኛ ክፍል ለፖሊስ አባልነት ሥልጠና ወደ ወሎ ክፍለ አገር አመሩ።

ከስድስት ወር የፖሊስ ሥልጠና በኋላ ተመርቀው ወደ ሥራ ተሰማሩ።

በ1953ዓ.ም ግን ሻምበል ጉታ የተለየ ዕድል ገጠማቸው።

ይሰሩበት ከነበረው የፖሊስ ማርሽ ባንድ ብቁ ሆነው ስላልተገኙ ለኮማንዶ ሥልጠና ለሦስት ወር ተላኩ።

ያኔ የኮማንዶ ሥልጠናውን የሚሰጡት እስራኤላውያን ነበሩ።

ይህ ሥልጠና አቶ ጉታን ለመልካም ዕድልም ለፈተናም ጋበዛቸው።

ኔልሰን ማንዴላ ለመጠበቅ ኃላፊነት መረከብ

ኔልሰን ማንዴላ በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት፣ ከስድሳ ዓመታት ገደማ በፊት ለወታደራዊ ሥልጠና ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር የሕይወት ታሪካቸውን በሰነዱበት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ የጓደኛቸውን ስም ይዘው፣ ጋዜጠኛ እንደሆኑም ነበር የተነገረው።

ማንዴላ የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ በሚሰለጥንበት አዲስ አበባ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ነው ሥልጠናውን የወሰዱት።

ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ ለሥልጠና ከመምጣታቸው በፊት ፓርቲያቸው ኤኤንሲ ከፖለቲካ ተሳትፎ በተጨማሪ የወታደራዊ ክንፍም አቋቁሞ ነበር።

“አፄ ኃይለ ሥላሴ ከእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ጋር ጥሩ ወዳጅ ስለነበሩ፣ በከፍተኛ ምስጢር ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሥልጠና እንዲወስዱ ለጄኔራል ታደሰ ብሩ ትዕዛዝ ተላለፈ። ለዚህም ደግሞ ሁለት አሠልጣኞች እና ሁለት ጠባቂዎች በምስጢር እንዲመደብላቸው ታዘዙ” ይላሉ ሻምበል ጉታ።

አንድ ቀን ለሻምበል ጉታ አዛዣቸው እንደሚፈልጋቸው ይነገራቸዋል።

እርሳቸውም ወደተጠሩበት ቢሮ ሲደርሱ መቶ አለቃ ፈቃዱ ወንድሙ እና 50 አለቃ ደበበ እሸቴ ቢሮ ተቀምጠው እየጠበቋቸው ነበር።

እርሳቸወም በወታደራዊ ሥርዓት ሰላምታ ሰጥተው የሚቀጥለውን ትዕዛዝ ሲጠብቁ ጄኔራል ታደሰ መጡ።

“ጄነራል ታደሰ ‘ከእዚህ በኋላ ከፍተኛ ምስጢር የሚፈልግ፣ ኃላፊነት ይሰጣችኋል። አንድ ትልቅ እንግዳ ወደ አገራችን መጥቷል። በዚህ ካምፕ ውስጥ ምስጢራዊ ቦታ ተዘጋጅቶለታል። ስለዚህ ለእናንተ የተሰጠው ይህንን ትልቅ ሰው የመጠበቅ ኃላፊነት ነው’ አሉን።”

በዚህ መልክ ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔ፣ የማንዴላ አሠልጣኝ፣ መቶ አለቃ ፈቃዱ ወንድሙ ረዳት አሠልጣኝ፣ ሹፌር እና የማንዴላ አስተርጓሚ ሆነው ይመደባሉ።

ሻምበል ጉታ ዲንቃ እና 50 አለቃ ደበበ እሸቴ፣ በፈረቃ ማንዴላን እንዲጠብቁ ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ኃላፊነት ተሰጣቸው።

በነጋታው ጄኔራል ታደሰ ብሩ በራሳቸው መኪና፣ ማንዴላን ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚገኘው ወደ መኮንኖች ክበብ ማምጣታቸውን አቶ ጉታ ያስታውሳሉ።

ኔልሰን ማንዴላን የመግደል ሴራ

ማንዴላ ማንነታቸውን ለመሰወር ስማቸውን እና ሙያቸውን በመቀየር ጥረት ቢያደርጉም የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግሥት መሪዎች ግን ዱካቸውን አነፍንፈው ደርሰውበታል።

እናም የማንዴላ ዕቅድ ከመንገድ ለማስቀረት በሚል ዕቅድ አውጥተው፣ በጀት በጅተው ተወካዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ።

ተወካዮቻቸው ደግሞ ማንዴላን የመግደል ዕቅድ አዘጋጅተዋል። ዕቅዳቸውም ማንዴላ በሚተኛበት ቦታ፣ በገመድ አንቆ የሚገድል ሰው በብር መግዛት ነበር።

ለዚህ ደግሞ ዐይናቸውን ሻምበል ጉታ ዲንቃ ላይ ነበር የጣሉት።

እርሳቸውን ለማባበል ከፍተኛ ገንዘብ ማቅረብ ሌላም መደለያ ማመቻቸት ጀመሩ።

“ያኔ ለሦስት ወር ኮማንዶ በእስራኤላውያን ስንሰለጥን፣ አብርሃም የሚባል ሰው ከኤርትራ የመጣ ጓደኛዬ ነበር። አብረንም እንሰለጥን ስለነበር በጣም እንዋደዳለን። ለካ እርሱ ይሰልለን ነበር። ማንዴላ እዚህ መኖሩ እና የእርሱ ጠባቂ መሆኔን በሆነ መልኩ አቀውቋል።

“አንድ ቀን ፒያሳ ጠርቶ ምሳ ልጋብዝህ አለኝ። ያን ቀን የእኔ ተራ እንዳልሆነ ያውቃል። ስለዚህ ጣይቱ ሆቴል ተገናኝተን ምሳ ከበላን በኋላ ከሁለት ሰዎች ጋር አስተዋወቀን፤ አንድ ነጭ እና አንድ ጥቁር።”

በልተው ጠጥተው ካበቁ በኋላ አብርሃም ለሻምበል ጉታ ያስደነገጣቸውን ነገር ይነግራቸዋል።

“እንግዲህ ጉታ፤ እኔና አንተ ጓደኛሞች ነን። ከዚህ የወታደር ሥራ የሚገላግለን አንድ ነገር ተገኝቷል። ትቀበላለህ ወይ? ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም ሎተሪ ደረሰህ ወይ? ብዬ ጠየቅኩት፤ ከዚያ አብርሃም ጉዳዩ በአንተ እጅ ነው። ካወቅንበት ማድረግ እንችላለን፤ ስለዚህ ቃል ግባልኝ አለ።

“እኔም የምችለው ከሆነ እሺ አልኩት። ‘እንደዚያ ከሆነ የምትጠብቀውን ሰው በመስኮት ገብተህ በተማርከው የኮማንዶ ስልት አንቀህ ትገድለዋለህ፤ ከሞተ በኋላ ሬሳውን ሁለት ጊዜ ፎቶ ታነሳዋለህ፤ ለዚህ ደግሞ ካሜራ ይሰጥሃል። ከዚያ በኋለ ከጦር ካምፕ ውጪ አንድ ቦታ በተዘጋጀ መኪና ሌሊት በሞያሌ በኩል እንወጣለን’ ብሎ እጅግ የሚያስደነግጥ ነገር ነገረኝ።”

ሻምበል ጉታ ግድያውን ፈጽመው ወደ ፈለጉበት የአውሮፓ አገር ሄደው እንዲኖሩ፣ በተጨማሪ ደግሞ የ2000 ፓውንድ የገንዘብ ስጦታ ተዘጋጅቶላቸዋል።

የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በዕቅዱ ተስማምተው 2000 ፓውንዱን እና ካሜራውን ተቀብለው ቀጥታ ወደ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ቤት አመሩ።

የግድያው ሴራ መክሸፍ

“ያኔ ከፒያሳ እስከ መርካቶ የሚኬደው በጋሪ ስለነበር ጋሪ ይዤ፣ ከዚያ በእግሬ በፍጥነት ወደ ጄነራል ታደሰ ቤት ነው ያመራሁት። ከዚያ ለኔልሰን ማንዴላ የግድያ ሴራ እንደተዘጋጀ እና እኔም ተስማምቼ እንደመጣሁ ነገርኳቸው።

“ጄነራል ታደሰ ሊያምኑኝ አልቻሉም። ኔልሰን ማንዴላ እዚህ መኖሩን በምን አወቁ የሚለው ጥያቄ ሆኖባቸዋል መሰለኝ። ነገ ማታ እርሱን ገድዬ በተዘጋጀ መኪና በሞያሌ በኩል ለመውጣት ዕቅድ እደያዝንና የምንገናኝበት ቦታ ደግሞ ከጦር ካምፑ 500 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጫካ ውስጥ መሆኑን ነገርኳቸው።”

ይህንን ለመቀልበስ ጄኔራል ታደሰ ጊዜ አልፈጀባቸውም።

ስለዚህ ምስጢራዊ ኦፕሬሽን ለማካሄድ ሁለቱ የማንዴላ አሠልጣኞች እና ጠባቂዎችን ሰበሰቡ። ከዚያም ዕቅድ አወጡ። እቅዳቸውም ፈቃደ ወንድሙ እና ደበበ እሸቴ በተባለው ቦታ ቀድመው በመገኘት በደፈጣ ይጠብቃሉ።

ሌሎች ሁለት ወታደሮች ደግሞ ሻምበል ጉታ ዲንቃ የተያዙ አስመስለው እጃቸውን በካቴና በማሰር ቀጥታ ሰዎቹ ወደ ሚጠብቁበት ቦታ ይወስዷቸዋል።

በሻምበል ጉታ እና አብርሃም ስምምነት መሰረት ኔልሰን ማንዴላ ሌሊት ተገድለው በዚያው ሌሊት በሞያሌ በኩል ወደ ውጪ ይጠፋሉ።

ሻምበል ጉታ ሃሳባቸውን እንዳይቀይሩ ቤተ ክርስትያን ሄደው እንዲምሉላቸው አብርሃም መጠየቁን ያስታውሳሉ።

ሻምበል ጉታ ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ቤት ከተመለሱ በኋላ 12 ሰዓት ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ለአብርሃም ማሉለት።

ወዲያው ግን ፈጣሪያቸውን በሐሰት ስለማሉ ይቅር እንዲላቸው ተማጽኗቸውን ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።

ጄኔራል ታደሰ ብሩ እንደመከሯቸውም ማንዴላን ገድለው ከሰዎቹ ጋር የሚገናኙበት ሰዓት ሲደርስ ሁለቱ ወታደሮች ሻምበል ጉታን ይዘው ከእነዚያ ሰዎች ጋር የሚገናኙበት ቦታ ወሰዷቸው።

በተመሳሳይ ሰዓት በቦታው የነበሩ ወታደሮች ሁለቱ የውጭ ዜጎች እና አብርሃምን በቁጥጥር ስር አዋሉ።

ሰዎቹ ሻምበል ጉታ ነው ያስያዘን እንዳይሉ ሻምበል ጉታም ያን ሌሊት አብረዋቸው እስር ቤት አደሩ።

“ጄኔራል ታደሰ ያዘጋጁት ምስጢራዊ ኦፕሬሽን በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ ማንዴላም ከሞት ተረፈ።”

የማንዴላ የግድያ ሙከራ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር መድረሱ

ሻምበል ጉታ እንዳሉት ማንዴላ ላይ የግድያ ሙከራ ሴራ መክሸፉን በጄኔራል ታደሰ ብሩ በኩል ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ደረሳቸው።

ይህንን ሙከራ ያከሸፈው ጉታ ዲንቃ የተባለ ወታደር መሆኑንም ጃንሆይ ሰሙ።

ይህ ምስጢር እንዳይወጣ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና ጄኔራል ታደሰ ዝምታን መረጡ።

ሁለቱ የውጭ አገር ዜጎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ተደረገ።

አብርሃም ደግሞ በወታደራዊ ሕግ መሰረት ከደረጃው ወርዶ ወደ ጠረፍ ተላከ።

ሻምበል ጉታ ዲንቁም ለዋሉት ውለታ፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የማዕረግ እድገት ቢሰጣቸው የግድያ ሴራው ወሬ ሌሎች ጆሮ ይደርሳል፣ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ በሚል ታለፉ።

ሻምበል ጉታ “ያኔ ብሩን ወስጄ የፈለግኩት አገር ሄጄ መማር እችል ነበር። ግን ማንዴላን በጣም እወደዋለሁ፤ ማንዴላ ለነጻነት ስለሚታገል እኛም ያኔ ሜጫ እና ቱለማ ውስጥ ስለ ነጻነት አንዳንድ ነገር እንፈልግ ነበር።

“ሌላ ደግሞ አዛዤ በጣም ይወደኛል። አምኖኝ ይህንን ሥራ ሰጠኝ፤ ጄኔራል ታደሰ ደግሞ መጀመሪያ ለዚህ ሥራ ሲመድቡኝ የመከሩኝ ነገር ልቤን አሸነፈ” በማለት ማባበያውን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

አክለውም “ ያኔ. . .ዛሬ የምትጠብቁት ሰው ትልቅ ሰው ነው። አንድ ቀን ስለ እርሱ አውቃችሁ እርሱን በመጠበቃችሁ ትኮራላችሁ አሉን። እኔም ማንዴላን ገድዬ የአገሬን ስም ማሰጠፋት አልፈለግኩም” በማለት ለምን ማንዴላን መግደል እንዳልመረጡ ይናገራሉ።

'ጄኔራል ታደሰ 250 ብር ሸለሙኝ'

ሻምበል ጉታ ማንዴላን ከሞት በማትረፋቸው ጄኔራል ታደሰ ሸለመዋቸዋል።

“ጠርተውኝ ‘አንተ ታሪክ ነው የሰራኽው’ አሉኝ። ‘ድሮም አንተን አውቅሃለሁ፣ አንተ ጀግና ነህ። አሁን ደግሞ ከልጆቼ መካከል እንደ አንዱ ነው የማይህ’ በማለት ከኪሳቸው ወስጥ 250 ብር አውጥተው ሸለሙኝ።”

ሻምበል ጉታ አክለውም ጄኔራል ታደሰ ከግለሰቦቹ የተገኘውን 2000 ፓውንድ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።

“ያኔ ጄኔራል ታደሰ ብሩ አባታቸው በጦር ሜዳ የሞቱ ልጆችን የሚያሳድግ ድርጅት ኃላፊ ነበሩ። ወ/ሮ ውዴ የምትባል ሥራ አስኪያጅ ነበረች። ጄኔራል ታደሰ 2000 ፓውንዱን መንዝረው አንድ ሳያስቀሩ ለድርጅቱ እንዲውል በማለት ለእርሷ ነበር ያስረከቡት። ካሜራውን ግን የት እዳስቀመጡት አላውቅም” ይላሉ።

ሻምበል ጉታ በ1981 ጡረታ እስኪወጡ ድረስ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ተሰልፈው አገራቸውን አገልግለዋል።

የስምንት ልጆች አባት የሆኑት የ87 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው ሻምበል ጉታ በትዳር 60 ዓመታትን ቆይታዋል።