ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤላውያን ለጋዛ የሚሄድ የእርዳታ ጭነቶችን በማገድ የእህል ከረጢቶችን ቀደው በተኑ
ለተቃውሞ የወጡ እስራኤላውያን ወደ ጋዛ የሚሄዱ የእርዳታ መኪኖችን በማገድ የተጫኑ ምግቦችን አውርደው መንድ ላይ በመወርወር እና የእህል ከረጢቶችን ቀደው በተኑ።
እስራኤላውያኑ ይህንን የፈጸሙት በትናትናው ዕለት እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራት በምትገኘው ዌስት ባንክ ነው።
ከዮርዳኖስ የመጡት እርዳታ የጫኑት መኪኖች ከኬብሮን በስተምዕራብ ታርኩሚያ የፍተሻ ጣቢያ እያቀኑ ነበር ተብሏል።
እርዳታው በከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ጠኔ ለተመቱ ፍልስጤማውያን የሚውል ነበር።
ዋይት ሃውስ ይህንን ጥቃት አውግዞ የእርዳታ ጭነቶቹን መዘረፍ “አሳፋሪ ስራ” ሲል ገልጾታል።
ከተቃውሞው ጀርባ ያለው ቡድን እስራኤላውያን ታጋቾች በጋዛ አለመለቀቃቸውን ለመቃወም የተደረገ ነው ማለቱ ተዘግቧል።
በተቃውሞ ሰልፉ የነበሩ ግለሰቦች የእርዳታ መኪኖቹ የጫኗቸውን ሳጥኖች መሬት ላይ ሲጥሉ እና በእግራቸው ሲረግጧቸው የሚያሳዪ ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ ድረገጾች ተሰራጭተዋል።
አንዳንድ ቪዲዮዎች ደግሞ ተሽካርካሪዎችን ሲያቃጥሏቸው የሚያሳዩ ሲሆን ቢቢሲ የእነዚህን ቪዲዮዎች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጀቸው ትዛቭ 9 የተሰኘ ቡድን ነው።
የቀኝ ክንፍ አክራሪ እንደሆነ በእስራኤል ሚዲያ የተገለጸው ይህ ቡድን እስራኤላውያን ታጋቾች እስካልተለቀቁ ድረስ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ያሉ ፍልስጤማውያን እርዳታ መድረስ የለበትም ብሎ ያምናል።
በተቃውሞው ላይ የነበረች ሃና ጊያት የተባለች ግለሰብ “ታጋቾቹ በጤና እና በህይወት እስኪመለሱ ድረስ” ምንም አይነት እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት የለበትም ብላለች።
ትዛቭ 9 በበበኩሉ የአንዳንድ ተቃዋሚዎቹን ድርጊት ውድቅ በማድረግ “ከንቅናቄያችን እሴት ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል” በሚል መግለጫ ማውጣቱን ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።
ነገር ግን “ታጋቾቹ እስኪመለሱ ድረስ ምንም እርዳታ አለማሳለፋችን ውጤታማ እና ተግባራዊ እርምጃ ነው” ሲል አክሏል።
የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የተቃዋሚዎቹ ድርጊት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ገልጸው ዋይት ሃውስ ያለውን ስጋት ከእስራኤል መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየከፋ እና ከፍተኛ ረሃብ ሊነሳ እንደሚችልም የተለያዩ አለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።