የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር 'ያልተፈቀደ መረጃ' ይፋ የሚያደርጉ መገናኛ ብዙኃንን እንደሚከለክል አስጠነቀቀ

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፒት ሄግሴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን ጋዜጠኞች በባለሥልጣናት ያልተፈቀደ መረጃን ላለማውጣት መስማማት እንዳለባቸው አለበለዚያ መስሪያ ቤቱን በሚመለከት መረጃ እንደሚከለከሉ አሳወቀ።

ይህ እርምጃ በቅርብ ከተወሰዱ አዲስ እገዳዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ጋዜጠⶉች በመከላከያ መስሪያ ቤቱ ያላቸውን እንቅስቃሴንም ለመገደብ ፍላጎት አለ።

ሚኒስቴሩ ማስጠነቀቂያውን ያወጣው ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ መረጃዎች ሾልከው በመውጣታቸው ነው።

የጦር ሚኒስትር የሚል አዲስ ማዕረግ የተሰጣቸው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው እንዳሉት፤ "መገናኛ ብዙኃን ፔንታጎንን አይመሩትም። ጋዜጠኞች ከዚህ በኋላ በፀጥታ ተቋም አዳራሾች መዟዟር አይፈቀደላቸውም። መለያችሁን አጥልቃችሁ ሕጉን ተከተሉ፤ አሊያም ወደ ቤታችሁ ሂዱ" ብለዋል።

አዲሱ ክልከላ ለጋዜጠኞች በጽሑፍ የተላከ ሲሆን፤ጋዜጠኞች የፔንታጎን የዘገባ ፈቃዳቸው እንዳይሰረዝ መፈረም አለባቸው።

መስሪያ ቤቱ "ተጠያቂነትን እና በሕዝብ ያለውን አመኔታ ለማሳደግ ለግልፀኝነት ያለው ቁርጠኝነት የተጠበቀ ነው" ብሏል።

ይሁን እንጂ ያለው ሚኒስቴሩ "መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ ከመሆናቸው በፊት ሚስጢራዊ ቢሆኑም እንኳ የጦር ሚኒስቴር መፍቀድ አለበት" በማለት አስጠንቅቋል።

መመሪያውን የሚፈርሙ ጋዜጠኞች ብሔራዊ ደኅንነት ተብለው የተለዩ መረጃዎችን ወይም እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር የተጣለባቸውን መረጃዎች "ያልተፈቀዱ መረጃዎችን ማውጣት፣ ለማውጣት መሞከር ወይም አሳልፎ መስጠት" እንዲገነዘቡት ይጠይቃል።

የፔንታጎን ዋና ቃለ አቀባይ ሿን ፓርኔል ለጋዜጠኞች የወጣው አዲስ መመሪያ በአገሪቱ ሁሉም የጦር ሰፈሮች ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል።

"ሚስጢራዊ መረጃዎችን ለመጠበቅ እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ እና በፔንታጎን የሚሰሩ ሥራዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ መመሪያው መሠረታዊ ነው" ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ሄግሴት በቅርቡ በየመን የቦምብ ድብደባን በሚመለከት ለጋዜጠኛ መረጃውን ሳያውቁ መስጠታቸውን ተከትሎ ሚስጢራዊ መረጃ አያያዛቸው በተመለከተ ጫና ገጥሟቸዋል።

ባለፈው ሰኔ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ አሜሪካ የፈፀመችው ጥቃትን በሚመለከት ሾልኮ የወጣ የደኅንነት መረጃ ለሕዝብ ይፋ ከሆነ መረጃ ጋር ተጣርሶ በመገኘቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጥርስ እንዲነክስ አድርጎታል።