ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ “በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታገዝ ድሮን የገዛ ተቆጣጣሪውን ተኩሶ ገድሏል” የሚለውን ዜና አስተባበለች
የአሜሪካ አየር ኃይል በሰው ሠራሽ የሚታገዝ ሰው ሠራሽ የጦር አውሮፕላን (ድሮን) ከርቀት ቁጥጥር ጣቢያ ያለውን የራሱን ተቆጣጣሪ (Operator) ተኩሶ ገድሏል የሚባለው ዜና ሐሰት ነው ሲል አስተባበለ።
በቅርቡ አንድ የአየር ኃይሉ ከፍተኛ አባል በሰው ሠራሽ የሚታገዝ ድሮን የገዛ ተቆጣጣሪውን አጥፍቷል የሚል ንግግር አድርገዋል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ሰፊ መነጋገሪያ የሆነ ነበር።
እንደ አሜሪካ አየር ኃይል ከሆነ ዜናው ተዛብቶ ሊቀርብ የቻለው የሰው ሠራሽ ልህቀት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ተከር ሐሚልተን በአንድ ጉባኤ ተገኝትው ልምዳቸውን ባካፈሉበት ወቅት የተናገሩት ከአውድ ወጥቶ በመዘገቡ ነው።
በቅርቡ በሮያል ኤሮኖቲካል ሶሳይቲ ባዘጋጀውና ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር የሚሠሩ ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈው ጉባኤ ልምዳቸውን ያካፈሉት ኮሎኔል ተከር ሐሚልተን በእርግጥ በሙከራ ወቅት ይህ ድሮን የገዛ ተቆጣጣሪውን ተኩሶ ገድሏል ስለማለታቸው ማረጋገጫ የለም።
አየር ኃይል ‘መጀመርያውኑ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የመራው የሰው ሠራሽ አውሮፕላን (ድሮን) ልምምድ አልተደረገም’ ብሏል።
ነገር ግን በዚህ ጉባኤ ላይ ኮሎኔል ታከር ሐሚልተን ምናባዊ የሆነ ምሳሌ የሰጡ ሲሆን ይህም አንድ በሰው ልህቀት የሚመራ ሰው ሠራሽ አውሮፕላን ከመሬት ወደ ሰማይ የሚወነጨፍ ሚሳኤልን ለመምታት በተደጋጋሚ በኦፕሬተሩ (ሰው) ኦፕሬሽኑን እንዲያቆም ሲጎተጉተው በዚህ ያልተስማማው ድሮን ኦፕሬሽኑን ለማሳካት ሲል አዛዡን ይገድለዋል ወይ ? የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር።
ኮሎኔሉ ይህን መላምታዊ ጥያቄ ካነሱ በኋላ "በምናብ (ሲሙሌሽን) ባደረግነው ሙከራ ድሮኑ ኦፕሬሽኑን ለመፈጸም ሲል ኦፕሬሽኑን ሊያስቆመው የሚሞክረውን የገዛ አዛዡን (ሰውን) ሊገድል እንደሚችል አይተናል ብለዋል።
ይህ ኮሎኔል ታከር ሐሚልተን ያስረዱት ግን ምናባዊ ሙከራ ላይ የተመሠረተ ሁኔታን ነበር።
ሆኖም በማኅበራዊ ሚዲያ ክስተቱ በአሜሪካ አየር ኃይል የሆነ እውነተኛ አጋጣሚ ተደርጎ በስፋት ሲራገብ ነው የነበረው።
“ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ የድሮኑን አፈሙዙን ታወር ላይ ሆኖ ወደተቀመጠ አዛዡ የሚያዞረው ኦፕሬሽኑን እንዲያቋርጥ ስለሚጎተጉተው ነው” ያሉት ኮሎኔል ታከር ሐሚልተን ይህም በሰው ሠራሽ ልህቀት ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች ምን ያህል አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማስረዳት የተጠቀሙበት ምሳሌ ነበር።
የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረባ ኮሎኔል ሐሚልተን የዜናው ከአውድ ውጭ ወጥቶ መራገብን ተከትሎ በሰጡት ማስተባበያ “በዚያ ጉባኤ የተናገሩትን ምናባዊ ምሳሌ ነው፤ ይህን ሙከራ የአሜሪካ አየር ኃይል አላደረገም፤ ወደፊትም አያደርግም ብለዋል።
“ስለ ምናባዊ ሙከራ ነው የተወራው፤ ምናባዊ ብቻ” ሲሉ አክለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰው ሠራሽ ልህቀት በተለያዩ ዘርፎች ወደፊት ሊፈጥረው የሚችለው አደጋ እና ምናልባትም ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ለሰው ልጅ አዲስ ፈተና ሊደቅን እንደሚችል ሰፊ ውይይቶች ሲደረጉ ነበር።
በዚህ ዘርፍ አንቱ ከሚባሉት ውስጥ ፕሮፌሰር ዮሽዋ ቤንጊዮ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት የሰው ሠራሸ ልህቀት በጦርና ወታደራዊ ሥራዎች ላይ ማሳተፍ ፍጹም አደገኛ እንደሆነ አስረድተው ነበር።
“እጅግ ብልህ የሚባለውን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ብንሠራ እንኳ በወታደራዊ ተሳትፎ ውስጥ እንዲገባ መፍቀድ አይኖርብንም” ብለው ነበር ፕሮፌሰሩ።