በአማራ ክልል በመከላከያ እና በታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ገለጸ

ባሕር ዳር

በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩን እና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ መንግሥት በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እያካሄደ ያለውን “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታ እና ተጽእኖ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ጋር በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን አመልክቷል።

በተለይም በሰሜን ሸዋ ውስጥ በሚገኙት በሸዋ ሮቢት፣ በአርማኒያ፣ በአንጾኪያ ገምዛ እና በማጀቴ አካባቢዎች “በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መኖሩን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት የደረሰ መሆኑን ገልጾ፣ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የተዘጋ መሆኑን እንዳረጋገጠ ኢሰመኮ አሳውቋል።

ይህ ግጭት የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የአማራ ብልጽግ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ በታጣቂዎች ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

ከፍተኛ ባለሥልጣኑ የተገደሉት አሁን ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ግጭት ተፈጥሮባቸዋል የተባሉት አካባቢዎች በሚገኙበት በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ መሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን በመመለስ ላይ ሳሉ መሆኑ ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልል መስተዳድር ተከሰተ ስለተባለው ግጭት እና ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

አቶ ግርማ የሺጥላ ከመገደላቸው ከሳምንታት ቀደም ብሎ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን ህልውና በማብቃት በፌደራል እና በክልል መከላከያ እና ፖሊስ ውስጥ እንዲካተቱ ያወጣው ዕቅድ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የመንግሥትን ውሳኔ የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደው ለቀናት የቆየ ውጥረት ተከስቶ ነበር።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን “መርተዋል ወይም አስተባብረዋል የተባሉ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ” ሰዎች እንደታሰሩ ኢሰመኮ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ ከባድ ጥሰቶችን የሚያስከትሉ በመሆናቸው ሁሉም ወገኖች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት እንዲፈቱ፣ ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እና ንግግሮች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

አክሎም ስለደረሱ ጉዳቶች አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም በማናቸውም ሁኔታ የሚፈጸሙ እስራቶች ሕግን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን መንግሥት እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል።