የ2017 የአዲስ አበባ ከተማ በጀት ከቀደመው ዓመት በ68.3 ቢሊዮን ብር የበለጠ ሆኖ ቀረበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ሳምንት ለተጀመረው የ2017 በጀት ዓመት የሚውል 230.39 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ለከተማዋ ምክር ቤት አቀረበ።

ለአዲሱ በጀት ዓመት የተያዘው ገንዘብ የከተማ አስተዳደሩ በ2016 ጥቅም ላይ ካዋለው ዋና እና ተጭማሪ በጀት የ68.3 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያለው ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2017 ዓ.ም. እንዲውል ባቀረበው በጀት ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው የካፒታል ወጪ እንደሆነ የከተማዋ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለ2017 ከተያዘው በጀት ውስጥ 62 በመቶው የተያዘው ለካፒታል ወጪዎች እንደሆነ የገለጹት አቶ አብዱልቃድር፤ ከበጀቱ ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች የተመደበው 38 በመቶው እንደሆነ አስረድተዋል።

ኃላፊው፤ “በከተማዋ በጣም ከፍተኛ የሆነ የካፒታል ፕሮጀክት ተመርቆ ወደ ሥራ ሲገባ በባህሪው የመደበኛ ወጪን የማሳደግ ዕድሉ ሰፊ ነው። ይህ ታሰቢ ከተደረገ የመደበኛው ወጪ ድርሻ መጨመር ነበረበት” ሲሉ የካፒታል ወጪ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው በመደበኛው ላይ ገደብ በመደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በ2013 ዓ.ም. 61 ቢሊዮን ብር የነበረው የከተማዋ በጀት ባለፉት ዓመታት በአራት እጥፍ ገደማ ለማደግ የፈጀበት አምስት ዓመት ብቻ ነው። በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያ ያጸደው 140.29 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህ የበጀት መጠን ከ2015 ጋር ሲነጻጸር የ40.2 በመቶ ዕድገት ነበረው።

ይሁንና በሚያዝያ ወር ላይ የከተማዋ ምክር ቤት ተጨማሪ 21.74 ቢሊዮን ብር በማጽደቁ፤ በበጀት ዓመቱ ጥቅም ላይ የዋለውን አጠቃላይ በጀት 162.03 ቢሊዮን ብር ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ለከተማዋ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ያለው የ2017 በጀት ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 42.1 በመቶ ዕድገት ያለው ነው።

የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልቃድር እንደሚናገሩት የከተማው ካቢኔ የ68.3 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው በጀት ያቀረበው፤ ሦስት ታሳቢዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

አቶ አብዱልቃድር በበጀት ዕቅዱ ውስጥ ታሳቢ እንደተደረገ የጠቀሱት ቀዳሚው ጉዳይ “የከተማዋ ኢኮኖሚ በምን ያህል ያድጋል?” የሚለውን ነው። በዚህ ታሳቢ ውስጥ በበጀት ዓመቱ ሊሰበሰብ የሚችለው ታክስ እንደሚካተት አክለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሊዝ በሚቀርብ መሬት ላይ “የተደረገው ማሻሻያ” በቢሮ ኃላፊው የተጠቀሰው ሁለተኛው ጉዳይ ነው። በዚህ መንገድ በሊዝ ከሚቀርብ መሬት የሚገኘው ገቢ በበጀት ዝግጅት ውስጥ ታሳቢ መደረጉን አንስተዋል።

አቶ አብዱልቃድር፤ “በተለይ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ [በሊዝ] ሊቀርቡ የሚችሉ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ነው። እነዚህ እና በመሬት ቢሮ ውስጥ የተደረጉ ማሻሻያዎች ሥራዎች የመሬትን አቅርቦት ከማሳደግ ጋር ተያይዞ የሚሠሩት ሥራዎች ይኖራል ተብሎ ታሳቢ ይደረጋል” ብለዋል።

በበጀቱ ዝግጅቱ ውስጥ ታሳቢ እንደተደረገ የተገለጸው ሌላኛው ጉዳይ ነዋሪዎች ለማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በሚጠየቁት የክፍያ መጠን ላይ የሚደረግ ማስተካከያ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ ለሚሰጡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የሚጠየቀው ክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት ከሚወጣው ወጪ አንጻር “እዚህ ግባ” የማይባል እንደሆነ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

“በአንዴ ሁሉንም የሚወጣውን ወጪ ይተካ ቢባል ከባድ ነው። ስለዚህ የሕብተሰረቡን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ማስተካከያ ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል” ሲሉ በከተማ አስተዳደሩ ለሚሰጡ አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ ላይ ጭማሪ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

እነዚህን ታሳቢዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀው የ2017 ዓ.ም. በጀት በከተማዋ ምክር ቤት ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱልቃድር፤ በተያዘው ሐምሌ ወር አጋማሽ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።