በአሜሪካ ኔቫዳ በረሃ ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ ግዙፍ ባዕድ ነገር ታየ

የፎቶው ባለመብት, Las Vegas Police
በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት ውስጥ በሚገኝ በአንድ በረሃማ ቦታ ምንነቱ ያልታወቀ ግዙፍ ባዕድ ነገር መታየቱ ተዘገበ።
ይህን የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ረዥም እና አንጸባራቂ ነገርን ያገኘው የላስ ቬጋስ ፖሊስ ነው።
ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በስፍራው የታየው ነገር ምንነትን በተመለከተ ብዙ ያልተረጋገጡ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ፖሊሶች ሰዎች ተራራ የሚወጡበት አካባቢ ላይ የጠፋን ሰው በመፈለግ ላይ ሳሉ ይህን ባዕድ ነገር ማግኘታቸው ተገልጿል።
“ብዙ እንግዳ ነገሮችን እንመለከታለን . . . እስቲ ይህን ተመልከተቱ!” ሲል የላስ ቬጋስ ፖሊስ የባዕድ ነገሩን ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አውጥቶታል።
ይህ ምንነቱ ያልታወቀ ግዙፍ ግዑዝ ነገር ከዚህ ቀደም እአአ 2020 ላይ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ከታየው ባዕድ ነገር ጋር ተመሳሳይነት አለው ተብሏል።
ፖሊስ ባጋራው ምሥል ላይ ይህ ከላስ ቬጋስ ከተማ በቅርብ ርቀት ከሚገኝ ስፍራ የተገኘው ረዥም አንጸባራቂ ነገር ወጣ ገባ በሆነ መሬት ላይ ቆሞ ታይቷል።
“እንዴት እዚህ ስፍራ ሊገኝ ቻለ?” ሲል የላስ ቬጋስ ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ጠይቋል።
ከአራት ዓመት በፊት የሄሊኮፕተር አብራሪ በአሜሪካ ዩታህ በረሃ ውስጥ ተመሳሳይ ቅርጽ ያለው ባዕድ ነገር ከተመለከተ በኋላ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በተመሳሳይ ወቅት ተመሳሳይ ነገር በአውሮፓዊቷ ሮማኒያ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ በካሊፎርኒያ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ተሳሳይ ቅርጽ ያለው ይህ አንጸባራቂ ነገር ተገኝቷል።
እነዚህን ባዕድ ነገሮች በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። አንዳንዶች ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ወይም ባዕድ አካላት ምንነቱ ያልተለየውን ነገር ተክለውት ሊሆን ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው።
ሌሎች ደግሞ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ወይም በምስጢር መያዝ የፈለጉ ግለሰቦች የሚተክሉት የጥበብ ሥራ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት ይሰጣሉ።
ቢሆንም ግን ከየትኛውም ወገን ይህ ነገር በትክክል ምን እንደሆነ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ አልወጣም።












