ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ላይ ቅናሽ ታየ
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ በምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታየ።
መቀለ የሚገኝ ጋዜጠኛ በተለይ ለቢቢሲ እንደዘገበው የጤፍ ዋጋን ጨምሮ የእህልና ሌሎች ዋጋ ንረቶች አሁን ድንገተኛ ቅናሽ አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ጋዜጠኛው ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪዎች ስምምነቱ እንዳስደሰታቸው እና በበጎ እንደተመለከቱት ተናግረዋል።
ብዙዎች ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢው እንደታዘበው ያነጋገራቸው በርካታ ሰዎች መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
የሰላም ስምምነቱ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የእህል እና የጥርጥሬ ገበያ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። በተለይ ቅናሹ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ በይበልጥ ተስተውሏል።
ቀደም ሲል የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 14ሺህ ብር የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ዜናን ተከትሎ ወደ 8ሺህ ብር ዝቅ ብሏል።
ስንዴም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ9ሺህ ብር ወደ 3ሺህ ወርዷል።
በተመሳሳይ የዘይት፣ የስኳር እና የበርበሬ ዋጋም መጠነኛ ቅናሽ እንደታየበት የመቀለ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
መቀለ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተዘዋውሮ እንደታዘበው ከሆነ የበርካታ ሰዎች ዋናው መነጋገሪያ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው።
የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሁለት ልጆች እናት ወ/ሮ ራሔል አባይ በሰላም ስምምነቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
“...ጦርነቱ በሚደረግበት ቦታ የምንኖረው እኛ ነን። መሬት ላይ ምን እንዳለ የምናውቀው እኛ ነን። አሁን ቢያንስ የድሮን ጥቃት ሳያሳስበን መንቀሳቀስ ጀምረናል” ብለዋል ወ/ሮ ራሔል።
ጋዜጠኛው እንዳለው ከሆነ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ወ/ሮ ራሔል ያለ አመለካከት ነው ያላቸው።
የ32 ዓመቱ በላይ ታከለ የመቀለ ነዋሪ ሲሆን፣ በሰላም ስምምነቱ ዙርያ ተጠይቆ ሲመልስ “እኛ የትግራይ ሕዝቦች እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላም መኖርን ነው የምንሻው። ጦርነቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን እኛ ነን የምናውቀው። አሁን የምንሻው ፈራሚዎቹ ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ነው።” ብሏል።
መቀለ የሚገኘው ጋዜጠኛ ያነጋገራቸው በትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ አማራ እና ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ እንዲከፈቱና የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ይሻሉ።
ከሰላም ስምምነቱ ጋር ብዙ ነዋሪዎችን እያነጋገረ ያለው የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ሕገ መንግሥቱ መከበር እንዳለበት ቢያምኑም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ይህም የሆነው ባለፉት ሁለት ዓመታት መከላከያ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸማቸው ነው ይላሉ።
ተስፋዬ አድሃኖም በመቀለ ከተማ በአዲ ሐቂ ነጋዴ ሲሆን ወደ ክልሉ የገባው “ወራሪው የኤርትራ ሠራዊት መቼ ነው ከአገራችን የሚወጣው” ሲል ጠይቋል። ጨምሮም፣ “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለምን በኤርትራ ጉዳይ ዙሪያ ዳተኛ እንደሆነ አይገባኝም” ብሏል።
ይህ በእንዲህ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት በሰላም ስምምነቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞና ጥርጣሬ ከመግለጽ አልተቆጠቡም። በተለይም የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ የሚዋጥላቸው አልሆነም።
በተለይም በስምምነቱ ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መውጣት እንዳለበት በማያሻማ ሁኔታ መገለጽ ነበረበት የሚል ቅሬታን ያሰማሉ።
ጋዜጠኛው ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመቀለ ሰማይ አሁን ሰላም በመሆኑና የድሮን ጥቃት ስጋት ገሸሽ በማለቱ ነዋሪዎች መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ወደ ገበያም ያለ ስጋት እየወጡ ነው።
ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በተለይ በትግራይ ክልል ላይ ከባድ ጠባሳን ያሳረፈ ሲሆን፣ የሸቀጦች እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉም መሠረታዊ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተው ቆይተዋል።