በካናዳ እና ሕንድ መካከል ያለው ውጥረት ተካሮ ዲፕሎማቶቻቸውን እስከ ማባረር ደረሰ

ጀስቲን ትሩዶ እና ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ, የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ እና የሕንዱ ናሬንድራ ሞዲ

በሰሜን አሜሪካዊቷ አገር ካናዳ እና በእሲያዊቷ አገር ሕንድ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተካሮ አንዳቸው የሌላኛውን ዲፕሎማት ከአገር አባረሩ።

በሁለቱ አገራት መካከል ቁርሾ የተፈጠረው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ የሕንድ የዘር ግንድ ያለው የካናዳ ዜጋ ካናዳ ውስጥ መገደሉን ተከትሎ ከግድያው ጀርባ የሕንድ መንግሥት እጅ አለበት ካሉ በኋላ ነው።

ሃርዲፕ ሲንግህ ኒጃር የተባለው ግለሰብ ሰኔ 2015 ላይ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በምትባለው የካናዳ ግዛት ውስጥ ነበር መኪናው ውስጥ በጥይት ተመትቶ ተገድሎ የተገኘው።

ይህ የሲክህ ሃይማኖት መሪ ፊታቸውን በጭንብል በሸፈኑ ሁለት ግለሰቦች መገደሉን ፖሊስ በወቅቱ ይፋ ቢያደርግም በግድያው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ የለም።

ግለሰቡ በሕንዷ ፑንጃብ ግዛት ከሃሊስታን የተሰኘች ራስ ገዝ የሲክህ ግዛት ለመፍጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት ከሕንድ ተሰድዶ በካናዳ ይኖር ነበር።

ከሕንድ ውጭ የሚገኙ የሲክህ እምነት ተከታዮች ከሃሊስታን የተሰኘ ግዛት ለመመስረት የሚያደርጉት ጥረት በሕንድ መንግሥት ቀይ መስመርን እንደ ማለፍ የሚቆጠር ሲሆን የሕንድ መንግሥት የዚህን እቅንስቃሴ አባላትን በሽብር ወንጀል ይከሳቸዋል።

የሃርዲፕ ኒጃር ቤተሰብ አባላትም ግለሰቡ በአቋሙ እና በእንቅስቃሴው ምክንያት የግድያ ዛቻዎች ይደርሱበት እንደበረ ይናገራሉ።

ከሕንድ ውጭ ካናዳ በርካታ ሲህኮች የሚገኙባት አገር ስትሆን የቡድኑ አባለት እንደፈቃቸው በአደባባይ እየወጡ ድምጻቸውን ማሰማታቸው ሕንድን ሲያበሳጭ የቆየ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

የካናዳ መንግሥት በሃርዲፕ ግድያ ሕንድ እጇ አለበት ካለች በኋላ አንድ ከፍተኛ የሕንድ ዲፕሎማት ከአገር እንዲባረር ማድረጉን የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ለዚህ የካናዳ እርምጃ ምላሽ በሚመስል ሁኔታ ሕንድ የካናዳ ዲፕሎማትን ከዴልሂ አሰናብታለች።

ከሃርዲፕ ግድያ ሦስት ወራት በኋላ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በሃርዲፕ ኒጃር ግድያ የሕንድ መንግሥት እጅ እንዳለበት ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎች አሉ ብለዋል። ይህ የካናዳ መንግሥት አስተያየት የሕንድ መንግሥትን እጅጉን አስቆጥቷል።

ከሦስት ወራት በፊት የተገደለው የሲህክ ሃይማኖት መሪ

የፎቶው ባለመብት, SIKH PA

የምስሉ መግለጫ, ከሦስት ወራት በፊት የተገደለው የሲህክ ሃይማኖት መሪ

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳን ክስ “ተቀባይነት” የሌለው ነው ያለ ሲሆን ከዚህ ቀደም የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ተመሳሳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ካቀረቡ በኋላ ክሳቸው ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጓል ብሏል።

ሃርዲፕ ኒጃር ወደ ካዳና እአአ 1997 ካመራ በኋላ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አንቱታን ያተረፈ የሲህክ መሪ መሆን ችሏል። ሕንድ ይህን ግለሰብ ከፑንጃብ ግዛት በመገንጠል ካሊስታን የተባለ ነጻ ግዛትን ለማቋቋም ከሚታገውል ካሊስታን ታይገር ፎርስ ጋር ግንኙነት አለው በማለት እአአ 2020 ላይ አሸባሪ ስትል ፈርጃዋለች።

የሰሜን አሜሪካዋ እና የኢሲያዋ አገር አለመግባባት ውስጥ ከገቡ በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው ብለዋል።

ዩኬ ይህን መሰል ከባድ ክስ በተመለከተ ከካናዳ ጋር እየተነጋገርኩ ነው ያለች ሲሆን አሜሪካም የቀረበው ክስ እጅጉን እንዳሳሰባት ገልጻ፣ ለግሰለቡ ግድያ ተጠያቂ የሆኑት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብላለች።