የትግራይ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ በበጎ አድራጊው ወጣት ዐይን

በረከት መኮንን እና ጓደኞቹ ከመቀሌ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሃገረ ሰላም ተብላ ወደ የምትታወቀው አነስተኛ ከተማ የሄዱት በውጭ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ያሰባሰቡትን እርዳታ ለማከፋፈል ነው።

እርዳታውን ማከፋፈል ሲጀምሩ ግን አንዲት ሴት ከውጭ ሆና እልልታዋን ታቀልጠው ጀመር።

ከዚያም እርሱ እና ባልደረቦቹ፣ ‘ምንተፈጠረ? የምን ዕልልታ ነው?’ በማለት ጠየቁ።

የበረከት ባልደረቦች እና አብረው የነበሩ ጋዜጠኞች እርዳታው ከሚከፋፈልበት ወጣ ብለው ሁኔታውን መጠየቅ ጀመሩ።

ወደ ውጭ የወጡ ሰዎች እልልታ ያሰማችውን እናት ጨቅላ ሕፃን አዝላ አገኟት።

በጀርባዋ ካዘለቸው ሕፃን በተጨማሪ ሌላ ጨቅላ ሕፃን በእጇ ታቅፋለች።

የታቀፈቻት ልጅ ከባድ ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ በከባድ የጦር መሳሪያ ጥቃት የተገደለች ጓደኛዋ ልጅ ናት።

ይህች እናት እልል እያለች ‘የሃገረ ሰላም ሕዝብ እርዳታ አገኘ!’ ስትል ደጋግማ ድምጿን ከፍ አድርጋ ትናገራለች

የበረከት ባልደረቦች ይህች ሴት ከተረጂዎች ዝርዝር ውስጥ አለመሆኗን ያውቃሉ።

ለምን እንደምትጮህና እልል እንደምትል ስትጠየቅ “የሃገረ ሰላም ህዝብ እርዳታ በማግኘቱ” ስትል ትመልሳለች።

“አንቺኮ በተረጂዎቹ ስም ዝርዝር ውስጥ የለሽም። እንዴትስ ሊያስደስትሽ ይችላል?” ይሏታል።

“የሃገረ ሰላም ሕዝብ እርዳታ አገኘ ማለት እኔም እርዳታ አገኘሁ ማለት” ስትል መለሰች።

ይህንን ሁኔታ ጓደኞቹ ቀርፀው ባስቀሩት ቪድዮ ውስጥ እንደተመለከተና ውስጡ በሐዘን እንደተሰበረ የሚናገረው በረከት “ሴትየዋ እልልታ ስታሰማ የነበረው፣ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች እርዳታ ካገኙ እርሷም በልታ ማደር እንደምትችል ስላመነች ነው። ምክንያቱም እሷ በከተማዋ ውስጥ በልመና ነው የምትተዳደረው” በማለት ያስረዳል።

አክሎም “. . . ነዋሪዎች የሚበሉት ካጡ እሷም የሚሰጣት ሰው ልታገኝ አትችልም። ስለዚህ ሕዝቡ እርዳታ አገኘ ማለት እሷና ልጆቿም አይራቡም ማለት ነው” ሲል በሥራው ወቅት ያየውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለችግር የተጋለጡትን በመደገፍ የተጀመረ በጎ ፈቃደኝነት

“ቀዛሕታ” በመባል የሚታወቀው የቴሌቭዥን ፕሮግራም አቅራቢ በረከት መኮንን በትግራይ ያለውን ማኅበራዊ ቀውስ ለመቅረፍ ከተለያዩ አካላት የሚለገሱ እርዳታዎች በማስተባበር ላይ ከሚገኙት በጎ ፈቃደኞች መካከል አንዱ ነው።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እርዳታ በመሰብሰብ የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት የበጎ አድራጎት ሥራ ያከናውን ነበረ።

“ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው የትግራይ ሴቶች እገዛ እንዲውል ከአዲስ አበባ የተላከ ዕርዳታ መነሻ ሆኖኝ ነው ሙሉ በሙሉ ወደ ማስተባበሩ የገባሁት” ይላል።

አክሎም “የተላከውን እገዛ ይዘን የፆታዊ ጥቃት እና ሌሎች ጉዳቶች ሰለባ የሆኑትን ለማየት ከትንሳኤ መረዳጃ ማህበር አስተባባሪ ጋር ወደ አይደር ሆስፒታል ሄድን። በወታደሮች ይጠበቅ በነበረበት ጊዜ ነበር ደፍረን የሄድነው” ይላል።

በረከት በትንሳኤ መረዳጃ ማህበር በኩል የተላከውን እርዳታ ለማድረስና ተጎጂዎችን ለማየት ወደ ሆስፒታል ሲሄድ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ እንደጠበቀው ያስታውሳል።

“ብዙ ያልጠበቅኩት አሳዛኝ እና የሚያስለቅስ ነገር ነበረ ያየሁት። ሆስፒታሉ ውስጥ በከባድ መሳሪያ ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናት እና እናቶችን አግኝቻለሁ። በተለይም ወደ 50 የሚጠጉ ሕጻናት አሰቃቂ የጦር መሳሪያ ጉዳት ደርሶባቸው ሳይ ልቤ ተሰበረ” በማለት ይገልፃል።

በረከት በሆስፒታል ውስጥ ያሉ ተጎጂዎችን እንዴት መርዳት እንዳለበት ከራሱ ጋር ከተወያየ በኋላ ሁኔታውን በቪዲዮ በመቅረጽ ለመልቀቅ ወሰነ።

ወደ ሆስፒታሉ እየገባ የሚቀርፃቸው ቪድዮዎችም ከበርካታ በውጭ አገራት ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እና ሌሎች እገዛ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጋር አስተዋወቀው።

“ቪዲዮዎቹ ከተለቀቁ በኋላ ብዙ ሰዎች አወቁኝ። ለተጎጂዎች የሚደርስ ገንዘብ ይላክልኝ ጀመር። ይህንን ማድረግ የጀመርኩት በየካቲት 2013 ዓ.ም ስለሆነ ጊዜው በጣም አስቸጋሪ እና አስፈሪ ነበር። ሰዎች ይታሰሩና ይገደሉ ነበር። እኛ ግን ሥራውን በድፍረት አስቀጠልነው” ይላል በረከት።

“አስቸጋሪና ፈታኝ” ሲል በሚገልጸው ወቅት ላይ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የጀመሩት ለተረጂዎች ዕርዳታ የማሰባሰብ እና የማድረስ የበጎ አድራጎት ዛሬም ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ በወቅቱ እርዳታ ወደ ሆስፒታል ካደረሱላቸው ሕፃናትና ጎልማሶች መካከል ዛሬ ላይ በሕይወት የሌሉ እንደሚገኙባቸው ይናገራል።

ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ

ጦርነት ከተቀሰቀሰበት 2013 ጥቅምትወር መገባደጃ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአስከፊ ማኅበራዊ ችግር እና የኑሮ ሁኔታ ላይ ውስጥ መሆናቸውን በረከት ይናገራል።

ለእነዚህ የዕለት ምግብ በማጣታቸው ምክንያት ለበሽታና ለሞት እየተጋለጡ ያሉ ዜጎች እርዳታ ለማድረስ በእርዳታ ድርጅቶች ከሚደርገው ጥረት በተጨማሪ፣ ግለሰቦችና ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሌሎች አካላትም ለመርዳት እየጣሩ ነው።

በረከት በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ያለበትን ሁኔታ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው ይላል። “ምናልባት በአጭሩ ‘መጥፎሁኔታ ላይ ነው ያለው’ ማለት ይቻል ይሆናል። ሆኖም ግን ሕዝቡ ያለበት ሁኔታ አስከፊ ከሚባለው እጅግ የከፋ ነው ተብሎ የሚገለጽ ነው” በማለት ሁኔታውን ይስረዳል።

አክሎም “ስለሁኔታው ለመናገር ቃላት ያጥረኛል። ሕፃናት እና እናቶች በየቀኑ ይሞታሉ። ‘ነገ ይነጋል!’ በሚል አጉል ተስፋ የሚኖሩበት ሁኔታ ነው ያለው። ይቅርና ይዘንላቸው የምንሄደው እርዳታ ሰጥተናቸው ገና የእኛ ወደ አካባቢያቸው መሄድ ሲያዩ ምን ያህል ተስፋ እንደሚሰጣቸው በዐይኔ አይቼ ያረጋገጥኩት ሁኔታ ነው” ይላል።

እሱ እንደሚለው መሠረታዊ ሸቀጦች የሉም። የሚገኝ ከሆነም በጣም ውድ ነው። ለምሳሌ ጤፍ በኩንታል 17,000 ብር እየተሸጠ ነው። ባለ5 ሊትርዘይት እስከ 400 ብር እንገዛ ነበር ዛሬ ግን 2500 ብር ይሸጣል። መብራት ቢጠፋ እንኳን ሻማ መግዛት ተትቷል፤ ምክንያቱም መግዛት የሚቻል አይደለም።

በየቀኑ ስለሚያያቸው ነገሮች ለመናገር ቃላት እንደሚያጥሩት ያሚናገረው በረከት “በየዕለቱ የሚቀርቡ ‘ሕጻናት ሞት’፤ ‘እናቶች ሞት’፤ እና ‘መድኃኒት የለም’ የሚሉ ዜናዎች በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የማይወክሉ ቀላል መገለጫዎች ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ወገናቸው ከገባበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት እያደረጉ ላሉት እገዛ ምስጋናና ክብር ሊቸራቸው እንደሚገባ በማስታወስ በትግራይ ውስይ ያለውን የሚያገኛትን ከጎረቤት ጋር ተካፍሎ ለማደር የሚያደርገው ትብብር ያደንቃል።

የእርዳታ ድርጅቶች ወደትግራይ የሚልኩት ምግብ በቂ ነው ባይባልም፣ የሚገባው እርዳታ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እንዳይዳረስ ዋነኛ እንቅፋት እየሆነ ያለው የነዳጅ እጥረት መሆኑ በረከት ይገልጻል።

“በቀላሉ ለማስረዳት የእኔን ተሞክሮ ላንሳ። ከመቀለ ወደ ሽረ ዕርዳታ አድርሼ ለመመለስ ከ40,000 እስከ 50,000 ብር ለነዳጅ እና ለሌሎች ወጪዎች ያስፈልገኛል። ነዳጅ አይገኝም። ከተገኘም በሊትር እስከ 450 ብር ይሸጣል። የትግራይ አስተዳደርም ነዳጅ የለውም። በዚህ ምክንያት ዕርዳታው ከመቀለ ውጪ ማዳረስ በጣም ከባድ ነው።”

ለማን ምን ዓይነት እርዳታ ይሰጣሉ?

የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ትግራይን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ከትግራይ ተወላጆች እና ሌሎች ለጋሾች የተላከውን እርዳታ ለማድረስ ወደ ብዙ የትግራይ አካባቢዎች ተንቀሳቅሷል።

ከሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ 95 በመቶ የሚሆነው በውጭ አገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የሚልኩት ሲሆን ገንዘቡን የተለያዩ መሠረታዊ ፍላጎቶችን በመግዛት ወደ ተረጂዎቹ እንደሚያደርሱ በረከት ያስረዳል።

“ብዙ ጊዜ የምንሄደው ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ተጠለሉባት ሽረ እና አካባቢዋ ነው። ወደዚያ የምንሄደውም የዞኖቹ ተፈናቃዮች በብዛት በሽረ ከተማ ስለሚገኙ ነው” ይላል።

ለተፈናቃዮች ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችም እርዳታ ለማዳረስ ይሞክራሉ። መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎችም የእርዳታው ተጠቃሚዎች ናቸው።

በዚህ እገዛ የማዳረስ እንቅስቃሴ ውስጥ በተለያዩ የማይድኑ በሽታዎች ለተጠቁ በሽተኞች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ በረከት ይናገራል።

“መላው የትግራይ ሕዝብ ከባድ ችግር ውስጥ ስለሚገኝ በቤታቸው ውስጥ የተራቡ ብዙዎች ናቸው። ለዚህም ነው የቻልነውን ያህል ለማዳረስ የምንሞክረው” ብሏል።

ከለጋሾች ያሰባሰቡትን እርዳታ በመያዝ ከሀገረ ሰላም እስከ ደጉ ተምቤን፤ ከውቅሮ እስከ ሐውዜን፤ ከአክሱም እስከ አድዋ እና ሽሬ፤ ከሳምረ እስከ ግጀት በተለያዩ አካባቢዎች አዳርሰዋል።

በረከት እና ባልደረቦቹ ከሕብረተሰቡ እና ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች በሚያገኙት መረጃ መሠረት፣ እርዳታ ወደ ሚያደርሱባቸው አካባቢዎች ይንቀሳቀሳሉ። አልፎ አልፎም ለጋሾቹ “ወደዚህ አካባቢ አድርሱልን” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው እንደተባሉት ያደርጋሉ።

ነገር ግን “በነዳጅ እጥረት እና የመገናኛ ዘዴዎች ባለመኖር ምክንያት አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰቡ ክፍል ለመለየት ወይም ለመድረስ ተቸግረናል።

አንዳንዴ ለተረጂዎች እንመጣለን ብለን ቀጠሮ አስይዘን በነዳጅ ችግርም ክንያት እስከመቅረት እንደርሳለን። በችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች ‘እርዳታ ወደ አንተ እየመጣን ነው’ ብለን እንዲጠብቁን ነግረናቸው ሳንሄድ ስንቀር ልብን በሐዘን ይሰብራል” በማለት ያስረዳል።

በረከት እና ባልደረቦቹ የሚያስተባብሩትን ገንዘብ ለተጠቃሚዎችሲያደርሱ፣ የተወሰነውን በጥሬ ገንዘብ የሚያከፋፍሉ ሲሆን፣ አብዛኛውን ግን በዓይነት ነው የሚያቀርቡት።

“ከዚህ በፊት ሩዝ፣ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ፉርኖ ዱቄትና እና ስንዴ ገዝተን እናቀርብ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። በዚህም ምክንያት ለሕጻናት እና እናቶች አልሚ ምግብ በማቅረብ ላይ ትኩረት አድርገናል” ይላል በረከት።

ሆኖም ግን በለጋሾች ፍላጎት ወይም ጥያቄ መሰረት አስፈላጊ ነገሮችን ለችግረኞች እያደረሱ ነው። ከዚህ ባለፈም እንደ ብርድ ልብስ፣ የምግብ ማብሰያ እቃዎች፣ ጫማዎች፣ አልባሳት፣ ብርድ ልብሶች እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለግሰዋል።