የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አሜሪካ ለነጭ አፍሪካነሮች የተሻለ የጥገኝነት መብት ለመስጠት ማቀዷን ተቃወመ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፎቶ ከፍ አድርገው ይዘው፤ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከአጠገባው ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ግንቦት ላይ በዋይት ሀውስ በተገኙበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነጮች ተገድለዋል በሚል ሀሰተኛ ፎቶ አሳይተው ነበር

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ አሜሪካ ከነጭ አፍሪካነሮች ለሚቀርቡ የስደተኝነት ጥያቄዎች ቅድሚያ ለመስጠት መወሰኗን ተቃወመ። በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል የሚለው ክስ በሰፊው ውድቅ የተደረገ እና ተአማኒ ማስረጃ የሚጎድለው መሆኑን ገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል የሚለውን ትርክት ውድቅ የሚያደርግ እና በታዋቂ የአፍሪካነር ማኅበረሰብ መሪዎች የተጻፈ ይፋዊ ደብዳቤን በማሳያነት ጠቅሷል። ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ደቡብ አፍሪካ ነጮችን ወደ ሌላ ሥፍራ የማዛወር ዕቅዱን ዘረኛ ሲሉ ገልጸውታል።

ደብዳቤው አክሎም፤ ወደ አሜሪካ ለመዛወር ያመለከቱ ነጮች ቁጥር ጥቂት መሆኑ አፍሪካነሮች እየተሳደዱ ላለመሆኑ ማሳያ መሆኑን አንስቷል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በየዓመቱ የምትቀበለው ከፍተኛው የስደተኛ ቁጥር 7,500 ብቻ እንዲሆን የሚያደርገውን ውሳኔው ይፋ ያደረገው ሐሙስ ዕለት ነበር።

ይህ ቁጥር እስካሁን ይጣል ከነበረው ዓመታዊ ገደብ በእጅጉ ያነሰ ነው። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያስቀመጡት ዓመታዊ የስደተኞች ገደብ 125,000 ነበር።

እስካሁን ምን ያህል ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በአዲሱ የአሜሪካ አሠራር የስደተኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል የሚለው ግልጽ አይደለም።

የቅርብ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ የወንጀል ስታትስቲክስ መረጃዎች ነጮች ከሌሎች የዘር ቡድኖች በተለየ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን አያመለክቱም።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ ልዩ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ መንግሥት ያለ ካሳ መሬት መውሰድ እንዲችል የሚፈቅድ ሕግ አጽድቀው ነበር። ይህንን ተከትሎም ትራምፕ በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2025 መጀመሪያ ላይ በብዛት የደች እና የፈረንሳይ ዝርያ ላላቸው የደቡብ አፍሪካ ነጮች የስደተኝነት መብት አቅርበው ነበር።

ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ውስጥ ሰባት በመቶ ብቻ ድርሻ ያላቸው የደቡብ አፍሪካ ነጮች፤ በአገሪቱ አብዛኛውን የግል የእርሻ መሬት ይቆጣጠራሉ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተወሰኑ ቡድኖችን "የበላይነትን እያቀነቀኑ" እንዲሁም "የነጮች ተጎጂነት [ትርክትን] እያስተጋቡ" እንደሆነ በመግለጽ የተቹት በዋሽንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል መጋቢት ወር ላይ ከአሜሪካ መባረራቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ግንቦት ላይ በዋይት ሃውስ ኦቫል ኦፊስ የተገኙትን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማፎሳን ፊት ለፊት ተጋፍጠዋቸዋል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነጭ ገበሬዎች እየገደሉ እና "እየተሳደዱ" መሆኑን በመጥቀስ ፕሬዝዳንቱ በተገኙበት ከስሰዋል።

ትራምፕ፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገደሉ ነጮች አስከሬን በፕላስቲክ መቋጠሩን ያሳያል ያሉትን ፎቶም ከፍ አድርገው ታይተዋል። ይሁን እንጂ የፎቶው ባለቤት የሆነው የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ምሥሉ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተነሳ መሆኑን ገልጿል።

የትራምፕ አስተዳደር ፎቶው የተሳሳተ ነው ስለመባሉ ምንም አስተያየት አልሰጠም።

በተጨማሪም ዋይት ሃውስ፤ የተገደሉ ነጭ ገበሬዎችን መቃብር ሥፍራ ያሳያል ያለውን ቪዲዮ አጫውቶ ነበር። ነገር ግን በቪዲዮ ላይ የመቃብር ሥፍራ ተብሎ የቀረበው ቦታ በ2020 በተካሄደ ተቃውሞ ወቅት በበርካታ ዓመታት ውስጥ የተገደሉ ገበሬዎችን ለማሳየት የተተከሉ የመስቀል ቅርጾችን የሚያሳይ እንደሆነ ተጋልጧል።