'በዓለም ትልቁ' በተባለ የክሪፕቶከረንሲ ምዝበራ 6.7 ቢሊዮን ዶላር ያገኘችው ቻይናዊት ተፈረደባት

በዓለም ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ ምዝበራ በተባለ የወንጀል ድርጊት የተከሰሰች ቻይናዊት ተፈረደባት።

በክሪፕቶከረንሲ ያገኘችው የገንዘብ መጠን ወደ 6.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተገልጿል።

ዚሚን ኩዊን የተባለችው ሴት ጥፋተኛ መሆኗን በፍርድ ቤት አምናለች። ያዲ ዣንግ በሚል ተለዋጭ ስም የምትታወቀው ቻይናዊት በለንደን ሳውዝዋርክ ክራውን ፍርድ ቤት ቀርባ በሕገ ወጥ መንገድ ክሪፕቶከረንሲ በማግኘት ክስ ጥፋተኛ ተብላለች።

እአአ ከ2014 እስከ 2017 ድረስ በቻይና ሰፊ የምዝበራ ሰንሰለት በመዘርጋት ከ128,000 በላይ ሰዎችን ማጭበርበሯ ተገልጿል። ያገኘችውን ገንዘብ በክሪፕቶከረንሲ ማከማቸቷንም ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በግለሰቧ ላይ ምርመራ የተጀመረው እአአ በ2018 ሲሆን፤ ፖሊስ ቢያንስ 61,000 ቢትኮይን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል።

መርማሪዋ ኢዛቤላ ግሮቶ "ለአምስት ዓመታት ለፍርድ ሳትቀርብ ቆይታለች። ምርመራው ውስብስብና ብዙ አገራትን ያሳተፈ ነበር" ብለዋል።

ግለሰቧ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከቻይና ሸሽታ ዩናይትድ ኪንግደም ገብታለች። የተለያዩ ንብረቶችን በመግዛት የሰረቀችውን ገንዘብ በሕጋዊ መስመር ለማስገባት ስትሞክርም ነበር።

በቻይና ምግብ የምታመላልስ ጂያን ዌን የተባለች ሠራተኛ በወንጀሉ ስለተባበረቻት የስድስት ዓመት ከስምንት ወር እስራት ተፈርዶባታል።

የ44 ዓመቷ ጂያን ዌን ሬስቶራን የሚገኝበት ሕንጻ ውስጥ ከመኖር ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቤት ውስጥ ወደመኖር መሸጋገሯን ፖሊስ ገልጿል።

በዱባይ 500,000 ፓውንድ የሚያወጣ ንብረት መግዛቷም ተገልጿል። ግዢ የፈጸመችው በቢትኮይን መሆኑ እንደ ማስረጃ ቀርቦባታል።

'ላይፍዊክ' የተባለው የቻይና መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው በ2024 ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 75 የሆኑ ባለሃብቶች "በመቶ ሺ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ" አውጥተው ዚሚን ኩዊን ባስተዋወቀችው የኢንቨስትመንት አማራጭ ላይ ተሰማርተዋል።

ክሪፕቶከረንሲ በቻይና ያለውን ዕውቅና በመጠቀም ዕለታዊ ትርፍ እንደሚያገኙ ቃል ገብታ ነበር ገንዘብ ፈሰስ እንዲያደርጉ ያሳመነቻቸው።

ቻይናን የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ ቃል በመግባት ባለሃብቶችን ማሳመኗን ፖሊስ ገልጿል።

ነጋዴዎች፣ የባንክ ሠራተኞች፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞች እንዲሁም ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ ሳይቀሩ ኢንቨስት አድርገዋል።

የተመዘበሩት ሰዎች ራሷን 'የገንዘብ አምላክ' ብላ ስለምትጠራው ዚሚን ኩዊን እምብዛም እንደማያውቁ ተገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ ሮቢን ዌይል "ቢትኮይን እና ሌሎች ክሪፕቶከረንሲዎች በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መጠቀሚያ እየሆኑ ነው። ወንጀለኞች በሚዘርፉት ገንዘብ ለመጠቀም በክሪፕቶከረንሲ ገንዘብ ያዘዋውራሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም፤ "በዩኬ ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ ነው። ምን ያህል ወንጀለኞች እየተደራጁ እንደመጡ ያሳያል" ብለዋል።

ጉዳዩ አሁንም በፖሊስ እየተመረመረ ሲሆን ገንዘባቸው ከተወሰደባቸው ሰዎች አብዛኞቹ ገንዘባቸው በከፊል ተመልሶላቸዋል።