ታይዋን ግጭት እንደማታስነሳ፤ ሉዓላዊነቷንም ግን አሳልፋ እንደማትሰጥ ፕሬዝዳንቱ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ ቻይና ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ስለ ታይዋን ነጻነት ከተወያዩ በኋላ አስተያየት የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ላይ ቺንግ ቴ፤ ታይዋን ምንም ዓይነት ግጭት አትቀሰቅስም ነገር ግን ሉዓላዊነቷንም አሳልፋ አትሰጥም አሉ።

የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው ፕሬዝዳንት ዢ፤ ቻይና እንደ ግዛቷ አካል የምትቆጥራት ታይዋን ጉዳይ ቤጂንግ በምታደርጋቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ውስጥ "እጅግ ወሳኝ ጉዳይ" መሆኑን ለትራምፕ ነግረዋቸዋል።

ራሷን በራሷ የምታስተዳድረውን ታይዋንን ጉዳይ በአግባቡ አለመያዝ ወደ ግጭት ሊያስገባ እንደሚችል ገልጸውላቸዋል።

ትራምፕ ከቤጂንግ ጉብኝታቸው መልስ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "የሆነ ሰው ነጻ እንዲሆን አልፈልግም" ሲሉ ታይዋንን አስጠንቅቀዋል።

የታይዋን የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው አሜሪካ፤ የዴሴቷ ግዛት ራሷን የምትከላከልበትን አቅም የማቅረብ ግዴታ በሕግ ተጥሎባታል።

ትራምፕ በቃለ መጠይቃቸው፤ አሜሪካ ታይዋንን በተመለከተ የምትከተለው ፖሊሲ አለመቀየሩን ገልጸዋል። ከቻይና ጋር ግጭት ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉም ግን ግልጽ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ዢ በታይዋን ጉዳይ "እጅግ ጠንካራ" ስሜት እንደታየባቸው ለጋዜጠኞች የተናገሩት ትራምፕ፤ እርሳቸው ግን "በሁለቱም በኩል ምንም ቃል እንዳልገቡ" ገልጸዋል።

የአሁኑ የታይዋን ፕሬዝዳንት እና የቀድሞዋ መሪ ሳይ ኢንግ ዌን መንግሥታት ለዓመታት የተከተሉት አቋም ታይዋን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ስለምትቆጠር በመደበኛ ሁኔታ ነጻነታችንን ማወጅ አያስፈልገንም የሚል ነበር።

ፕሬዝዳንት ላይ ከሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በኋላ ቀጥተኛ ምላሽ በሰጡበት የፌስቡክ ጽሑፍ፤ "ምንም ዓይነት 'የታይዋን ነጻነት' የሚባል ጉዳይ የለም" ብለዋል።

"የታይዋን፤ ቻይና ሪፐብሊክ ሉዓላዊት፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊት አገር ናት" ሲሉ የጻፉት ፕሬዝዳንቱ፤ "የታይዋን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመላው ታይዋን ሕዝብ ፍላጎትን የተከተለ መሆን አለበት" ብለዋል።

ታይዋን ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ ራሱን የሚቆጥረው እንደ ሉዓላዊነት አገር ነው። በአንጻሩም ደግሞ በርካቶች አሁን ያለውን ከቻይና ያለመዋሃድም ሆነ በይፋ ነጻነትን ያለማወጅ አካሄድ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።

ቤጂንግ በታይዋኑ ፕሬዝዳንት ላይ ደስተኝ እንዳልሆነች በግልጽ አሳይታለች። ፕሬዝዳንቱን "ችግር ፈጣሪ" እና "ወሽመጥ ተሻጋሪ ሰላምን አጥፊ" ስትል ገልጻቸዋለች።

ፕሬዝዳንት ላይ ፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ታይዋን አትተነኩስም፣ ግጭቶች እንዲባባሱም አታደርግም፤ ነገር ግን በግፊት ምክንያት ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን፣ ክብሯን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ እና ነጻ የሕይወት ዘይቤዋን አሳልፋ አትሰጥም" ብለዋል።

"ታይዋን ሁልጊዜም በሁለቱም የወሽመጡ ጎኖች ባሉ ወገኖች መካከል ያለው ነባራዊ ሁኔታን በጽናት የምትከላከል እንጂ ሁኔታውን የምትቀይር ወገን አይደለችም" ሲሉም ጽፈዋል።

ታይዋን "ከቻይና ጋር በእኩልነት እና ክብር ላይ የተመሠረተ ጤናማ እና ሥርዓት ያለው ግንኙነት እና ውይይት ለማድረግ" ፈቃደኛ መሆኗንም አክለዋል።

ነገር ግን ቻይና "ዳግም መዋሃድን" በሽፋንነት በመጠቀም ታይዋንን አስገድዳ ወደ ንግግር ለማስገባት የምታደርገውን ሙከራ ውድቅ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።