ስለ ኢቦላ መታወቅ ያለባቸው ዋና ዋና ነጥቦች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ሲል አውጇል።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ኢቱሪ ግዛት በሚገኙት ሞንግዋሉ እና ሩዋምፓራ ከተሞች 246 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ እና 65 ሰዎች እንደሞቱ የአፍሪካ በሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ተቋም አስታውቋል።

ተቋሙ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር ውይይት አድርጓል። በሽታውን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ እንዲሁም ድንበር ላይ መደረግ ስላለበት ቁጥጥር መምከራቸውም ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2025 በማዕከላዊቷ ካይሲ ግዛት 45 ሰዎች በኢቦላ ምክንያት ሞተዋል።

ኢቦላ ምንድን ነው?

ኢቦላ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ የሆነ ተላላፊ በሽታ ነው። መጀመሪያ ላይ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ከፍተኛ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ጉሮሮ መከርከር ናቸው።

ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሲሰራጭ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ይከሰታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ እና ከሰውነታቸው ውጭ ደም ይፈስሳቸዋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምልክት የሚያሳዩት ከሁለት ቀናት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ኢቦላ እንደ ወባ እና ታይፎይድ ካሉ ሕመሞች ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች አሉት።

ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው የሚረጋገጠው በቤተ ሙከራ በሚደረግ ምርመራ ብቻ ነው።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለይቶ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1976 ሲሆን፤ በወቅቱ ወረርሽኙ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ተስፋፍቶ ነበር።

በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ ጋር የሚኖር ንክኪ ነው። ይህም ደም፣ ምራቅ፣ የወንድ የዘር ፈሳሽ፣ ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፣ ሽንት፣ ሰገራ እና ላብን ይጨምራል።

ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ የነካቸው ቁሳቁሶችም በሽታውን ያስተላልፋሉ። ዐይን፣ አፍንጫ፣ አፍ እና አንዳች ስንጥቅ ያለው የቆዳ ክፍል በመንካት ቫይረሱ ይተላለፋል።

የሌሊት ወፍ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጃርት እና ድኩላ በሽታውን የሚያስተላልፉ እንሰሳት ናቸው። ለምግብነት የሚታደኑ የዱር እንሰሳት ሥጋ ላይ ቫይረሱ ሊኖር ይችላል።

በኢቦላ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን መንካትም ለበሽታው ያጋልጣል።

በቅርቡ ኢቦላ የተከሰተው የት ነው?

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በከፍተኛ መጠን የኢቦላ ወረርሽኝ የተነሳው ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ሲሆን 2,300 ገደማ ሰዎች ሞተዋል።

በ2022 በኡጋንዳ በተከሰተው የሱዳን ኢቦላ ዝርያ ወረርሽኝ ምክንያት 164 ሰዎች ለኅልፈት ተዳርገዋል።

በ2014 በጊኒ፣ በላይቤሪያ እና በሴራ ሊዮን የተነሳው የኢቦላ ወረርሽኝ ከምንጊዜውም በላይ የከፋ ሲሆን ከ11,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ኢቦላን ማከም ይቻላል?

የኦቦላ ቫይረስ የተለያዩ ዝርያዎች አሉት። በዛየር ለሚገኘው የኢቦላ ዝርያ ክትባት ተገኝቷል።

የሱዳን የኢቦላ ዝርያን ጨምሮ ለሌሎችም የኢቦላ ዓይነቶች ክትባት ወይም መድኃኒት ለማግኘት ሳይንቲስቶች ምርምራቸውን ቀጥለዋል።

በሆስፒታሎች ውስጥ ሐኪሞች ለሕሙማን ድጋፍ ይሰጣሉ። የውሃ ጥምን መቁረጥ (rehydration)፣ እንደ ሶዲየም፣ ፖታሽየም፣ ካልሽየም እና ማግኒዥየም ያሉ ንጥረ ነገሮችን ማመጣጠን (electrolyte balance) እንዲሁም ደም በመለገስ በሕይወት የመትረፍ ዕድልን መጨመር ከሕክምናዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ኢቦላን እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወይም ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር አካላዊ ንክኪ አለማድረግ
  • የተጋለጡት ለዛየር የኢቦላ ዝርያ ከሆነ ክትባት መውሰድ
  • ወረርሽኙ በተነሳበት አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ እጅን አዘውትሮ መታጠብ
  • ሥጋን በአግባቡ አብስሎ መመገብ
  • በኢቦላ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን አለመንካት
  • ኢቦላ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወደ ሕክምና ተቋም ማምራት