ቀጥታ, ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ

የሁለቱ አገራት የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በአፋጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው፤ ካልሆነ አንዳች ነገራቸው እንኳ አይተርፍም” ብለው ዝተዋል። በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ዋናው ነገር ጊዜ ነው” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ መብቷ ላይ “እንደማትደራደር ወይም ከአቋሟ ፈቀቅ እንደማትል” ገለጸች

    የኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ መብት “ድርድር የሚደረግበት ወይም ከአቋም ፈቀቅ የሚባልበት ጉዳይ” እንዳልሆነ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ ኢስማኢል ባቃኢ ዛሬ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጦርነቱን ለመቋጨት በፓኪስታን አማካኝነት የሚደረገው ንግግር መቀጠሉን ገልጸዋል።

    ኢራን ባለ 14 ነጥብ የስምምነት ዕቅድ ወደ አሜሪካ ልካ እንደነበር ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ዋሽንግተንም ሆነ ቴህራን በዕቅዱ ላይ የራሳቸውን ሐሳብ ማንሳታቸውን ተናግረዋል።

    “የአሜሪካው ወገን ይህ [ባለ 14 ነጥብ] ዕቅድ ውድቅ መደረጉን ባለፈው ሳምንት በይፋ ቢያስታውቅም፤ ያቀረቧቸው ነጥቦች እና የማስተካከያ አስተያየቶች ዝርዝር ግን በፓኪስታን አማካኝነት ደርሶናል” ብለዋል።

    “ዕቅዳችንን በላክን ማግስት ከሌላኛው ወገን የቀረቡ ተከታታይ ዕቅዶች ደርሰውናል። ዕቅዶቹ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተገመገሙ ሲሆን የእኛ ምላሽም ቀርቧል። በፓኪስታን አማካኝነት የሚደረገው ድርድር ቀጥሏል" ሲሉም ንግግሩን የማስጀመር ሂደቱ ያለበትን አረስድተዋል።

    ይህም ቢሆን ግን ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ መብቷን ለድርድር እንደማታቀርብ ባቃኢ ተናግረዋል።

    "በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው፤ [ዩራኒየም የማበልጸግ] መብት ልንደራደርበት ወይም ከአቋም ፈቀቅ የምንልበት ጉዳይ አይደለም። ኢራን ዩራኒየም ለማበልጸግ ያላት መብት የኒውክሌር መሣሪያዎች ላለማስፋፋት በተፈረመው ስምምነት መሠረት እውቅና የተሰጠው ነው" ብለዋል።

    እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ኢራን የምትፈልጋቸው የድርድር ነጥቦች በግልጽ ተቀምጠዋል። እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ የኢራን ሀብቶች መለቀቅን በማሳያነት ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ "እናንተ እኛ [ለድርድር] ያስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ትናገራላችሁ፤ እኛ የመብት ጥያቄ እንደሆነ እንናገራለን” ብለዋል።

  2. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ላይ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ወታደራዊ አማራጮች ‘በሲቹዌሽን ሩም’ ሊሰበሰቡ መሆኑ ተዘገበ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ሊፈጸሙ ስለሚችሉ ወታደራዊ አማራጮች ለመወያየት ማክሰኞ ዕለት ከፍተኛ የብሔራዊ ደኅነት አመራሮቻቸውን ይሰበስባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አክሲዮስ ዘገበ።

    የአሜሪካው የዜና ምንጭ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፤ የፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደኅንነት ቡድን አባላት ስለ ኢራን ለመወያየት ቅዳሜ ዕለትም ተሰብስበው ነበር።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫምስ፣ የዋይት ሃውስ መልዕክተኛ ስቲፍ ዊትኮፍ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ነበሩ ተብሏል።

    ትራምፕ ለአክሲዮስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ከኢራን ጋን ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

    የኢራን የድርድር ዕቅድ ላይ የሚደረገውን ማሻሻያ እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ከቀናት በፊት ከቀረበው የተሻለ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል። ለድርድሩ ቀነ ገደብ ከማስቀመጥ ግን ተቆጥበዋል።

    “ስምምነት መፈጸም እንፈልጋለን። እንዲሆኑ የምንፈልገው ቦታ ላይ አይደሉም። እዚያ መረድስ አለባቸው ወይም ክፉኛ ይመታሉ፤ ያንን ደግሞ አይፈልጉም” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ከመጀመሪያው ዙር ድርድር በኋላ ንግግሩን ለማስቀጠል አልተገናኙም።

    አሸማጋይ ሆና እየተንቀሳቀሰች ያለቸው ፓኪስታን ቅዳሜ ዕለት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ቴህራን ልካ ነበር። ድርድሩን ለማስጀመር እሑድ ዕለትም ከኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ሲነጋገሩ ነበር።

  3. የእስራኤል ጦር ከኢራን ጋር ለሚኖር ሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑ ተዘገበ

    እስራኤል በቀጣይ በኢራን ላይ ሊፈጸም በሚችለው ጥቃት ውስጥ ሠራዊቷ ከአሜሪካ ጎን እንዲሳተፍ ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኑን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    ካን የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ስማቸው ያልተጠቀሰ የእስራኤል የደኅንነት ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ከጀመረች እስራኤል በዘመቻው ውስጥ በመሳተፍ የኢራንን “የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶችን” ዒላማ ታደርጋለች ብለዋል።

    ይህ ዘገባ የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እሑድ ዕለት በስልክ ከተወያዩ እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኢራን ከስምምነት ለመድረስ ያላት ጊዜ ወደ ማብቂያው እየተቃረበ መሆኑን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ካን ቴሌቪዥን እንደዘገበው በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ከግማሽ ሰዓት በላይ የቆየ ሲሆን፣ ከኢራን ጋር ሌላ ዙር ጦርነት ሊከሰት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተነገግረዋል።

    ሌላኛው የእስራኤል ቴሌቪዥን ቻናል 12 ደግሞ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት “ከኢራን ጋር ለሚደረግ አዲስ ጦርነት በሚደረግ ዝግጅት ጥላ ስር” መካሄዱን በመጥቀስ የእስራኤል ጦርም ለአዲስ ግጭት በሙሉ ተጠንቀቅ ላይ” መሆኑን ዘግቧል።

    በተጨማሪም ቻናል 13 የተባለው የእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ በርካታ የጭነት አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎችን ይዘው ወደ እስራኤል መግባታቸውን ዘግቧል።

    ዘገባው ጨምሮም የጭነት አውሮፕላኖቹ ጀርመን ውስጥ ከሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ተነስተው ባለፉት 24 ሰዓተት ቴል አቪቭ ውስጥ አርፈዋል።

  4. ኩዌት እና ኳታር በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት አወገዙ

    ኩዌት እና ኳታር በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች፤ ከኢራቅ የአየር ክልል በመነሳት ሳዑዲ አረቢያ ላይ የተሰነዘረውን የድሮን ጥቃት አወገዙ።

    ኩዌት፤ ይህ ድርጊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በባሕረ ሰላጤው መሠረተ ልማቶች ለመጠበቅ ያሳለፈውን ውሳኔ የሚጥስ ነው ብላለች።

    ሳዑዲ አረቢያ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ ለምትወስዳቸው እርምጃዎች ያላትን ድጋፍም ገልጻለች።

    ኳታር በበኩሏ ድርጊቱን "ተቀባይነት የሌለው ጥቃት" እና የሳዑዲን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ ስትል ገልጻዋለች።

    ሁለቱም አገራት ለሪያድ ያላቸውን ሙሉ አጋርነት የገለጹ ሲሆን፤ ሳዑዲ ግዛቷን እና ዜጎቿን ለመጠበቅ የምትወስዳቸውን ማናቸውንም እርምጃዎች እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

    ኳታር እና ኩዌት መግለጫ ያወጡት ሳዑዲ አረቢያ የአየር መከላከያ ሥርዓቶቿ ሦስት የጥቃት ድሮኖችን መትተው መጣላቸውን ካስታወቀች በኋላ ነው።

  5. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኒውክሌር ጣቢያ አቅራቢያ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እሑድ ዕለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዋ አቅራቢያ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት እሳት እንዲነሳ ማድረጉን አስታወቀች።

    ክስተቱን “አደገኛ [የግጭት] መባባስ” ስትል የጠራችው ኤምሬቶች፤ ባለሥልጣናት ጥቃቱ ከየት እንደተፈጸመ እየመረመሩ መሆኑን ገልጻለች።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ድሮኖች ወደ ኤምሬቶች ግዛት የገቡት “በምዕራብ የድንበር አቅጣጫ" በኩል ነው።

    ሁለቱ ድሮኖች እንደተጠለፉ እና ሦስተኛው ግን በአቡ ዳቢ የሚገኘው የባራካህ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ "ከውስጣዊው ቅጥር ግቢ ይዞታ ውጭ" የሚገኝ የኤሌክትሪክ ጄነሬተርን እንደመታ ተገልጿል። እሳቱም የተነሳው በዚሁ ምክንያት ነው ተብሏል።

    በጥቃቱ ጉዳት አለመድረሱን የሚናገሩት ባለሥልጣናቱ፤ በአካባቢው የራዲዮሎጂካል ደኅንነት ደረጃ ላይም ተጽዕኖ አለማሳደሩን ገልጸዋል።

    የኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክስተቱን "ተቀባይነት የሌለው የጥቃት ድርጊት" በማለት ጠርቶታል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለማንኛውም ጠበኛ ድርጊት ምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ "ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ተቋማትን ዒላማ ማድረግ ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነት እና የሰብአዊ ሕግ መርሆዎች ጥሰት ነው" ብሏል።

    የኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ "የአገሪቱን ደኅንነት ለማዳከም የሚደረጉ ማናቸውንም ሙከራዎች በጽናት እንደሚጋፈጥ" አስታውቋል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ድሮኑ ከየት እንደተተኮሰ እስካሁን አልገለጹም። ከዚህ ቀደም ግን ኤምሬቶች ከጦርነቱ መነሳት ወዲህ በነዳጅ እና በኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶቿ ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጀርባ ኢራን እንዳለች በመግለጽ በተደጋጋሚ ከስሳለች።

    የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ በክስተቱ “ከፍተኛ ስጋት” እንደገባቸው ተናግረዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የኤክስ ገጽ በወጣው መግለጫቸው፤ "የኒውክሌር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

  6. ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ።

    የሁለቱ አገራት የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ሲሆን፤ ትራምፕ “በአፋጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው፤ ካልሆነ አንዳች ነገራቸው እንኳ አይተርፍም” ብለው ዝተዋል። በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ዋናው ነገር ጊዜ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ትናንት እሑድ በስልክ መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።

    ቴህራን ጦርነቱን ለማቆም ያቀረበችው የሰላም ዕቅድ ላይ አሜሪካ ከስምምነት መድረስ አለመቻሏን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ዋሽንግተን የሰላም ዕቅዱ ተቀባይነት እንዲኖረው ጥረት ካላደረገች ውጤት እንደማይገኝ የኢራኑ መህር የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ያሳለፍነው ሳምንት ትራምፕ የሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም “በቋፍ ላይ ነው” ሲሉ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ መሆኑን ገልጸዋል።

    የኢራን የሰላም ዕቅድ “ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለው ትራምፕ ቢያጣጥሉም፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጊ “ምክንያታዊ እና ለጋስ” ነጥቦች እንዳቀረቡ ተናግረዋል።