የአውሮፓ ኅብረት በአሜሪካ ላይ የሚጥለውን የአፀፋ የንግድ ታሪፍ አዘገየ

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየን ጊዜውን ለመደራደር እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል

የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የአፀፋ ታሪፍ ለመጣል የነበረውን ዕቅድ እንደገና ማዘግየቱን የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን አስታወቁ።

ማክሰኞ ሊጀመር ታቅዶ የነበረው የአፀፋ የንግድ ታሪፍ እርምጃ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በብረት እና በአሉሚኒየም ላይ ለጣሉትን ታሪፍ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነበር።

የአውሮፓ ኅብረት፤ 21 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጡ የአሜሪካ ሸቀጦች ላይ ለመጣል ያቀደው የአፀፋ ታሪፍ ለመጀመርያ ጊዜ የታገደው መጋቢት ላይ ነበር።

ይህ መዘግየት እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ድረስ ተራዝሟል ሲሉ ቮን ደር ሌየን እሁድ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የንግድ ሚኒስትሮች ምላሽ በሚሰጡበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት ሰኞ ብራስልስ ውስጥ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ የሆነው ትራምፕ ከነሐሴ1 ጀምሮ በአውሮፓ ኅብረት ምርቶች ላይ የ30 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ማቀዳቸውን ለቮን ደር ሌየን ደብዳቤ ከፃፉ በኋላ ነው።

የንግድ አጋሮቹ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የአፀፋ ታሪፍ የሚጥሉ ከሆነ የሚቀመጥባቸውን የታሪፍ መጠን ከ30 በመቶ በላይ ከፍ እንደሚያደርጉት አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ቅዳሜ ምሽት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ አንዳንድ አገራት "አሁን በጣም ተበሳጭተዋል" ነገር ግን ታሪፉ "በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ዶላር" እያስገኘ ነው ብለዋል።

ቮን ደር ሌየን እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ዩናይትድ ስቴትስ በድርድር መፍትሄ እስካልተገኘ ድረስ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን የያዘ ደብዳቤ ልካለች። ስለሆነም የአፀፋ እርምጃዎቻችንን እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ድረስ እናራዝማለን።

"በተመሳሳይ ጊዜ፣ እኛ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንድንሆን ለመከላከያ እርምጃዎች መዘጋጀታችንን እንቀጥላለን።"

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት፤ የአውሮፓ ኅብረት "የድርድር መፍትሄን እንደሚመርጥ ሁል ጊዜ ግልፅ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

"ይህ አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ እና እስከ ነሐሴ 1 ድረስ ያለንን ጊዜ እንጠቀማለን" ሲሉም አክለዋል።

'የአውሮፓን ጥቅሞች ማስጠበቅ'

የአውሮፓ ኅብረት የንግድ ሚኒስትሮች ከዋሽንግተን ጋር በሚኖራቸው ድርድር ምን ዓይነት ጠንካራ አቋም እንደሚይዙ ለመምከር ሰኞ ብራስልስ ውስጥ ሊገናኙ ነው።

የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ላርስ ክሊንግቤል እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ከአሜሪካ ጋር "ኮስተር ያለ እና መፍትሄን ያማከለ ድርድር" አሁንም አስፈላጊ ነው። ይህ ካልተሳካ ግን የአውሮፓ ኅብረት "በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ሥራዎችን እና ንግዶችን ለማስጠበቅ ወሳኝ የመከላከያ እርምጃዎችን" መውሰድ ያስፈልገዋል ብለዋል።

"እጃችን የተዘረጋ ቢሆንም የሰጡንን ሁሉ አንቀበልም" ሲል ክሊንግቤል ለአንድ ዕለታዊ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የእርሳቸው አስተያየት የተሰማው ቅዳሜ ዕለት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአውሮፓ ኅብረት አገራትን ወክሎ የሚደራደረው የአውሮፓ ኮሚሽን "የአውሮፓን ጥቅም በቆራጥነት እንዲያስጠብቅ" ማሳሰባቸውን ተከትሎ ነው።

ከቅዳሜ ጀምሮ የትራምፕ አስተዳደር 27 አገራትን ባቀፈው በ24 አገራት እና በአውሮፓ ኅብረት ላይ የታሪፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።

ሚያዚያ 12 የዋይት ሐውስ የንግድ አማካሪ ፒተር ናቫሮ "90 ስምምነቶችን በ90 ቀናት" የሚል ግብ አስቀምጠው ነበር።

እስካሁን ድረስ ፕሬዚዳንቱ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከቬትናም ጋር ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ከሌሎች ጋር ድርድራቸውን ቀጥለዋል።