አሜሪካ የጣለችውን ከፍተኛ ታሪፍ ተፈፃሚነት በማዘግየት በአንዳንድ አገሮች ላይ አዲስ የታሪፍ ምጣኔ አስተዋወቀች

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥለውት የነበውን ከፍተኛ ታሪፍ ተፈፃሚነት አዘገዩ።

ፕሬዝዳንቱ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ለ14 አገራት የተጣለባቸውን አዲስ ቀረጥ የያዘ ደብዳቤ ልከዋል።

ይህ የታወጀው በገቢ ምርቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ታሪፍ የ90 ቀናት የእፎይታ ጊዜው ከመጠናቀቁ ከቀናት አስቀድሞ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማስፈራሪያቸውን ቀጥለው ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከነሐሴ 1/2025 ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆን የ25 በመቶ ታሪፍ የጣሉበትን ደብዳቤ ይፋ አድርገዋል።

የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት የንግድ ድርድር ለማድረግ ሲባል ገታ አድርገውት የነበረው ከፍተኛ ታሪፍ እ.አ.አ ሐምሌ 9 ጀምሮ እንዲተገበር ቀን ተቆርጦለት ነበር።

አዲሱ የተቆረጠው ቀን የመጨረሻው እንደሆነ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ትራምፕ፤ "ቋሚ ነው እላለሁ። ነገር ግን መቶ በመቶ አይደለም። ደውለው በሌላ መንገድ መሄድ ከፈለጉ ይህን ለማድረግ በራችን ክፍት ነው" ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አደም አሕማድ ሳሚዲን የንግድ ስምምነቶች ዓመታትን የሚወስዱ በመሆናቸው የታሪፉ መራዘም የሚያስገርም እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"እንደዚህ ዓይነት ስምምነቶች በአብዛኛው ዘርዘር ያሉ ናቸው" ያሉት ባለሙያው ምንም እንኳ ቬትናም ከዩናይትድ ኪንግደም በመቀጠል ከአሜሪካ ጋር የንግግድ ስምምነት ላይ ብትደርስም፤ ከሙሉ ስምምነት ይልቅ ንግግሮችን ለማቀላጠፍ "ሰፋ ያለ ማዕቀፍ" ነው ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰኞ ዕለት ትራምፕ አዲሱን የታሪፍ እቅዳቸውን የሚገልፅ ለ14 አገራት መሪዎች የላኩትን ደብዳቤ በማኅበራዊ የትስስር ገፅ በማጋራት፤ እንደየ አገራቱ ግንኙነት የታሪፍ ምጣኔው ማሻሻያ ይደረግበታል ብለዋል።

በደብዳቤው የተዘረዘሩት አብዛኞቹ የታሪፍ ምጣኔዎች ባለፈው ሚያዚያ ከወጣው ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፉ የአሜሪካ ንግዶችን ከውጭ ፉክክር በመጠበቅ፣ የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ እና ሥራ ይፈጥራል በሚል ይሞግታሉ።

ነገር ግን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እርምጃው በአሜሪካ የምርቶች ዋጋ እንዲያሻቅብ እና ንግድ እንዲቀዛቀዝ ያደርጋል የሚል ትችት ያቀርባሉ።

ጃፓን ባለፈው ዓመት 146 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በመላክ ከአውሮፓ ሕብረት፣ ሜክሲኮ፣ ቻይና እና ካናዳ በመቀጠል ለአሜሪካ አምስተኛዋ ምርት አቅራቢ አገር ስትሆን፤ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በመቀጠል ትራምፕ ምያንማር እና ላኦስ ላይ 40 በመቶ፣ ታይላንድ እና ካምቦዲያ 36 በመቶ፣ ሰርቢያ እና ባንግላዲሽ 35 በመቶ፣ ኢንዶኔዥያ 32 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 30 በመቶ፣ ማሌዥያ እና ቱኒዝያ ደግሞ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽግሩ ኢሽባ ሁለቱንም አገራት የሚጠቅም ስምምነት ላይ ለመድረስ መንግሥታቸው ንግግሩን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የተራዘመውን ቀነ ገደብ በመጠቀም ከአሜሪካ ጋር ንግግሯን እንደምታጠናክር ገልፃለች።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት የታሪፉ ተፈፃሚነት መራዘም የትራምፕን የዛቻ አቅም የቀነሰ ነው መባሉን አጣጥለዋል።

"የፕሬዝዳንቱ ስልክ ስምምነት ለመፈፀም በሚለምኑ የዓለም መሪዎች ጥሪ ተጨናንቋል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሚያዚያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጣሉትን ታሪፍ ሲያሳውቁ በፋይናንስ ገበያው መረበሽ ተፈጥሮ ነበር።