የአውሮፓ ኅብረት እና ሜክሲኮ በትራምፕ የተጣለባቸውን የ30 በመቶ ታሪፍ ተቹ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውሮፓ ኅብረት እና ሜክሲኮ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ ከነሐሴ 01/2025 ጀምሮ የሚፈፀም የ30 በመቶ ታሪፍ ለመጣል በመዛታቸው ብስጭታቸውን ገልፀዋል።

ሜክሲኮ የትራምፕን እርምጃ "ኢ ፍትኃዊ ስምምነት" ስትል የጠራቸው ሲሆን፤ ሉዓላዊነቷ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ደጋግማ ተናግራለች።

የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቫና ደር ሊይን በበኩላቸው አስፈላጊ ከሆነ "ተመጣጣኝ የአፀፋ እርምጃ" እንደሚወስዱ ዝተዋል።

ሁለቱም አካላት ከአሜሪካ ጋር ድርድራቸውን የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ግን ተናግረዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች አፀፋ ከወሰዱ ከዚህ በላይ ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ሳምንት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጃፓን፣ደቡብ ኮሪያ፣ካናዳ እና ብራዚል ምርቶች ላይ በሚቀጥለው ወር የሚፈፀም አዲስ ታሪፍ ጥለዋል።

አርብ ዕለት ትራምፕ ለአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቫና ደር ሊይን በፃፉት ደብዳቤ "ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የንግድ ግንኙነታችንን ለመምከር ዓመታት ነበሩን። እና አሁን በእናንተ ታሪፍ፣ታሪፍ አልባ እና የንግድ ፖሊሲዎች ምክንያት ከመጣው ረዥም እና ግዙፍ፣ የማያቋርጥ የንግድ ጉድለት አደጋ መራቅ አለብን" ብለዋል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ ግንኙነታችን የጋርዮሽ አይደለም" ሲል ደብዳቤው ያክላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለአውሮፓ ኅብረት እና ሜክሲኮ በተፃፈው በዚህ ደብዳቤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የንግድ አጋሮቹ በሚያስገቧቸው የአሜሪካ ምርቶች ላይ አፀፋዊ ታሪፍ ከጣሉ፤ በጣሉት ልክ ከ30 በመቶ በላይ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አንዳንድ አገራት "አሁን በጣም ተበሳጭተዋል" ካሉ በኋላ፤ ነገር ግን ታሪፉ "መቶ ቢሊዮኖች ዶላር እያስገኘ" ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የትራምፕ ትችት ተደጋጋሚ ዒላማ ነው።

ባለፈው ሚያዚያ በአባል አገራቱ ላይ የ20 በመቶ ታሪፍ መጣላቸውን አስታውቀዋል። በመቀጠልም የንግድ ድርድሮች ሲቀዛቀዙ የአውሮፓ ኅብረት ምርቶች ላይ ታሪፉን ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ ዝተዋል።

ዋሽንግተን እና ብራሰልስ ባለፈው ሳምንት ከተጠናቀቀው ቀነ ገደብ በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ ቢፈልጉም፤ እስካሁን ይፋ የሆነ እድገት የለም።

በአሜሪካ የንግድ ወኪል ቢሮ መረጃ መሰረት እ.አ.አ በ2024 ከአባል አገራቱ ጋር የአሜሪካ የንግድ ጉድለት 235.6 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ኧርሰላ ቫና ደር ሊይን የአውሮፓ ኅብረት "ከነሐሴ 1 በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ መስራቱን ለመቀጠል" ዝግጁነቱ አሁንም አለ ብለዋል።

"የአውሮፓ ኅብረትን ጥቅም ለመጠበቅ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንወስዳለን። አስፈላጊ ከሆነ ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ መውሰድን ጨምሮ" ብለዋል።

"በዓለም የአውሮፓ ኅብረትን የምጣኔ ሀብት አቅም የሚመጥኑ ጥቂት አገራት ብቻ ፍትኃዊ የንግድ አካሄድ እና ፍላጎት አላቸው" ሲሉም በመግለጫቸው አክለዋል።

27 አባል አገራት ያሉት ኅብረቱ ከዋሽንግተን ጋር ከቀነ ገደቡ በፊት ስምምነት የመድረስ ተስፋ እንዳለውም አስታውቋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በትራምፕ ታሪፍ "በጣም እንደማይስማሙ" ገልፀዋል።

ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የፈረንሳዩ መሪ የአውሮፓ ኅብረት "አሳማኝ የሆኑ የአፀፋ እርምጃዎችን ማዘጋጀቱን እንዲያፋጥን" የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

ለሜክሲኮ መሪ ትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ ሰሜን አሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ መናኸሪያ እንዳይሆን የሚያስፈልገውን እርምጃ ሜክሲኮ አልወሰደችም ሲሉ ከሰዋል።

"ድንበሩን ለማጠናከር ሜክሲኮ እየረዳችኝ ነው። ነገር ግን ሜክሲኮ ያደረገችው በቂ አይደለም" ሲሉ አክለዋል።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡዋም ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን መተማመን ገልፀዋል።

"ባልደረቦቻችን ባደረጉት ውይይት መሰረት ከዩናይትድ ስቴት ጋር ስምምነት፤ በእርጥም የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደርሳለን ብለን እናምናለን" ብለዋል።