ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕጻናት የተዘጋጀው የወባ መድኃኒት ጥቅም ላይ እንዲውል ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለጨቅላ ሕፃናት እና ለታዳጊዎች ተስማሚ የሆነው የመጀመሪያው የወባ መድኃኒት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ አገኘ።
መድኃኒቱ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ አገራት ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ በተለይ ለሕፃናት የተፈቀደ የወባ መድኃኒት የለም።
በምትኩ ለትላልቅ ልጆች የተዘጋጁ መድኃኒቶችን እንዲወስዱ ሲደረግ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከመጠን በላይ የመውሰድ አደጋን ያስከትላል።
በ2023 ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ወደ 597,000 የሚጠጉ ሰዎች በወባ ምከንያት ሞተዋል።
ከሞላ ጎደል ሁሉም ሞቶች የተመዘገቡት በአፍሪካ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስት አራተኛው የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ናቸው።
እስካሁን ድረስ ለልጆች ጥቅም ላይ የሚውሉ የወባ መድኃኒቶች የነበሩ ቢሆንም፣ ከ4.5 ኪሎ ግራም በታች ለሆኑ ጨቅላ ሕፃናት እና ታዳጊዎች ግን የተለየ ሕክምና አልነበረም።
ይልቁንም ለትላልቅ ሕጻናት ተብለው የተዘጋጁ መድኃኒቶችን እንዲወስዱ ሲደረግ ቆይቷል።
ነገር ግን ለታዳጊዎች የተዘጋጁትን መድኃኒቶች ለትናንሽ ሕጻናት በሚሰጥበት ወቅት ጉበታቸው ገና በማደግ ላይ ያለ በመሆኑ እና ሰውነታቸው መድኃኒቶችን በተለየ መንገድ ለሚያዋህድ ሕጻናት አደጋን ሊያስከትል ይችላል።
ይህንን ባለሙያዎች "የሕክምና ክፍተት" ብለው እንደሚጠሩት ይናገራሉ።
አሁን ኖቫርቲስ በተባለው የመድኃኒት ኩባንያ የተሠራው አዲስ መድኃኒት በስዊትዘርላንድ ባለሥልጣናት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፣ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው አህጉራት እና አገራት ውስጥ ሊከፋፈል እንደሚችል ተነግሯል።
ኖቫርቲስ መድኃኒቱን በአብዛኛው ትርፍን መሠረት ባላደረገ መልኩ ለማስተዋወቅ አቅዷል።
በጣም ትንንሾቹ፣ በጣም ተጋላጭ ናቸው
የኖርቫቲስ መድኃኒት አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቫስ ናራሲምሃን ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው ይላሉ።
"ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ወባን ለመከላከል በሚደረገው ትግል ሳይንሳዊ ግኝቶችን በጣም በሚፈልጉበት ቦታ ላይ ለማድረስ ያለ እረፍት እየሠራን ቆይተናል።
"ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በክሊኒክ ውስጥ የተረጋገጠ የወባ ሕክምና አዲስ ለተወለዱ ሕጻናት እና ለታዳጊ ሕጻናት በማዘጋጀት፣ ጨቅላ እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን እንኳን በመጨረሻ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረጋችን ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።
በአንዳንድ አገራት ኮአርተም ቤቢ ወይም ሪያሜት ቤቢ በመባል የሚታወቁት መድኃኒቶች በኖቫርቲስ ከሜዲስን ፎር ማላሪያ ቬንቸር ጋር በመተባባር ተሠርቷል።
ይህ ምርምር መጀመሪያ ላይ በብሪታንያ፣ በስዊትዘርላንድ እና በሆላንድ መንግሥታት እንዲሁም በዓለም ባንክ እና በሮክፌለር ፋውንዴሽን ይደገፍ ነበር።
በመድኃኒቱ ግምገማ እና ሙከራ ላይም ስምንት የአፍሪካ አገራት የተሳተፉ ሲሆን፣ መድኃኒቱን ለማግኘት ቀዳሚዎቹ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኤምኤምቪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርቲን ፊቸት ይህ በወባ የሚደርሰውን ከፍተኛ ኪሳራ ለማስቆም በመንገድ ላይ ያለ ሌላው ጠቃሚ እርምጃ ነው ብለዋል።
"ወባ በዓለም ላይ ገዳይ ከሆኑት በሽታዎች አንዱ ነው፤ በተለይ በልጆች ላይ። ነገር ግን በትክክለኛ ምርምሮች እና ትኩረት ሊወገድ ይችላል።"
"የኮአርተም ቤቢ መጽደቅ በሌላ መንገድ ችላ የተባሉትን የታካሚዎችን ለማከም በተመቻቸ መጠን አስፈላጊውን መድኃኒት ያቀርባል፤ እና በፀረ ወባ ዘመቻው ላይ ጠቃሚ አበርክቶ ይሰጣል።"
በሄርትፎርድሻየር ዩኒቨርስቲ የሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ማርቬሌ ብራውን ይህ የጨቅላ ሕጻናትን እና የታዳጊዎችን ሕይወት ለመታደግ እንደ ትልቅ እመርታ መታየት አለበት ብለዋል።
"በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በወባ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ ነው።
"በወባ ምክንያት የሚሞቱት ሕጻናት ቁጥር የበለጠ እየጨመረ የሚሄደው ከሲክል ሴል ጋር በተወለዱ ሕፃናት ላይ ሲሆን፣ ይህም በዋነኛነት በሽታን የመከላከል አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ነው።
"ከሕዝብ ጤና አንፃር ኖቫርቲስ ይህንን ለትርፍ እንዳይውል ማድረጉ በጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ላይ ያለ አለመመጣጠንን ለመቀነስ ይረዳል ።"















