ኮቪድ ከቤተ ሙከራ ሾልኮ ወጥቶ ሊሆን ይችላል ሲል ሲአይኤ ገለጸ

ጆን ራትክሊፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ኮቪድ ከቻይና ቤተ ሙከራ ሾልኮ የወጣ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው ሲል ገለጸ።

ከቤተ ሙከራ ሾልኮ ቫይረሱ ካመለጠ በኋላ ወደ እንሰሳት ተሻግሯል ተብሏል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ቫይረሱ በተፈጥሮ የተከሰተ ከመሆን ዕድሉ "ከምርምር ጋር በተያያዘ የሾለከ" የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ የሾሟቸው የሲአይኤ አዲስ ኃላፊ ጆን ራትክሊፍ ከወሰኗቸው የመጀመሪያዎቹ ውሳኔዎች አንዱ ግኝቱን ማስታወቅ ነው።

በቀድሞው የትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ነበሩ። ከውሃን የቫይረስ ምርምር ቤተ ሙከራ ቫይረሱ አምልጧል ብለው ከሚያምኑ መካከል ናቸው።

ቤተ ሙከራው የእንሰሳት ውጤት ከሚሸጥበት ገበያ 40 ደቂቃ ነው የሚርቀው።

የሲአይኤ አዲስ ኃላፊ እንዳሉት፣ ሲአይኤ በጉዳዩ ላይ አማካዩን መንገድ በመከተል አይዘልቅም።

"ከቻይና በብዙ ጉዳይ ያለውን ስጋት ማንሳት አለብኝ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሞተው የቫይረሱ መነሻ ሳይጠና ሊቀር አይችልም። የመጀመሪያ የኃላፊነት ውሳኔዬ ነው" ብለዋል።

ሲአይኤ መግለጫውን ሲያወጣ ስለ መረጃው "በአነስተኛ መጠን ነው እርግጠኛ የሆነው" ሲል ገልጿል።

ይህ ማለት ወደ ድምዳሜ የወሰደው መረጃ ጥልቀት የሚጎድለው ወይም እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃን የተመረኮዘ ነው ማለት ነው።

አንዳንዶች ቫይረሱ ያለ ሳይንቲስቶች ወይም ቤተ ሙከራ ጣልቃ ገብነት "በተፈጥሯዊ መንገድ" የተነሳና በእንሰሳት አማካይነት የተስፋፋ ነው ብለው ያምናሉ።

ከቤተ ሙከራ የሾለከ ነው የሚለውን መላ ምት በተለይ ሳይንቲስቶች አይቀበሉትም።

ይህንን መላ ምት የሚደግፍ በቂ ማስረጃ የለም ብለው ይከራከራሉ።

ቻይናም ይህ ሐሳብ የአሜሪካ "ፖለቲካዊ መጠምዘዝ" ነው ስትል አጣጥላዋለች።

እአአ በ2023 የሲአይኤ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ራይ ለፎክስ ኒውስ እንዳሉት "የቫይረሱ መነሻ ከቤተ መኩራ ጋር የተያያዘ" ሊሆን ይችላል።