ጨረር ሲነካቸው በረራቸው የሚስተጓጎል በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርባስ አውሮፕላኖች ታገዱ

ኤርባስ ወደ 6,000 የሚጠጉ ኤ320 አውሮፕላኖቹ እክል ስለገጠማቸው በረራ እንዳያደርጉ አገደ።

አውሮፕላኖቹ የፀሐይ ጨረር ሲነካቸው የበረራ ተቆጣጣሪ ኮምፒውተራቸው ላይ ችግር ስለሚከሰት ጉዞ ማድረግ እንደማይችሉ ኩባንያው አስታውቋል።

አውሮፕላን አምራቹ ባስተላለፈው ውሳኔ ምክንያት በመላው ዓለም በርካታ በረራዎች ዘግይተዋል።

ኤ320 አውሮፕላኖች ላይ የመተግበሪያ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ወደ በረራ እንደሚመለሱ ተገልጿል።

በረራዎች በመዘግየታቸው እና በመሰረዛቸው ምክንያት አየር መንገዶች ለደንበኞቻቸው ተከታታይ መረጃ እየሰጡ ነው።

ያለፈው ጥቅምት ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ እየበረረ የነበረ ኤ320 አውሮፕላን በድንገት እየተጓዘበት ከነበረው ከፍታ ወደታች ዝቅ በማለቱ ኤርባስ ምርመራ አካሂዷል።

በምርመራው መሠረትም የፀሐይ ጨረር የበረራ ተቆጣጣሪ ኮምፒውተሮችን ሥራ እንዳስተጓጎለ ደርሶበታል።

ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ እየበረረ የነበረው የጀትብሉ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በረራውን ከማቋረጡ በፊት 15 ሰዎች ተጎድተዋል።

ኤ320፤ ኤርባስ በቀዳሚነት ለገበያ የሚያቀርበው ምርት ነው። ኤ320 የገጠመው እክል በኤ318፣ ኤ319 እና ኤ321 አውሮፕላኖች ላይም ተስተውሏል።

ወደ 5,100 የሚጠጉ የኤርባስ አውሮፕላኖች በሦስት ሰዓት ውስጥ መተግበሪያቸውን እንደሚያሻሽሉ ተገልጿል።

የተቀሩት 900 አውሮፕላኖች ከተሠሩ ዓመታት ስለተቆጠረ ኮምፒውተራቸው በአዲስ መቀየር ይኖርበታል። ኮምፒውተራቸው እስከሚለወጥ ድረስም በረራ ማካሄድ አይችሉም።

ኤርባስ፤ የገጠመው እክል የደንበኞችን እና ተጓዦችን በረራ በማስተጓጎሉ ይቅርታ ጠይቋል።

የአቪዬሽን ባለሙያ ሳሊ ጌቲን "የገጠማቸው ችግር ያልተለመደ ነው። የተለያዩ አየር መንገዶች የተለያየ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ" ብለዋል።

ሉፍታንዛ፤ ኤርባስ አውሮፕላኖችን ከበረራ እንደሚያግድ ሲገልጽ፤ አንዳንድ አየር መንገዶች ግን የጎላ ችግር እንደማይገጥማቸው አስታውቀዋል።

ለምሳሌ ሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መስተጓጎል አልገጠመውም።

ብሪትሽ ኤርዌይስ ብዙም ጉዳት እንዳላስተዋለ ሲገልጽ፤ ዊዝ ኤር እና ኤር ኢንዲያ የመተግበሪያ ማሻሻያ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በአሜሪካ እና አንዳንድ አገራትም የምስጋና ቀን ስለሚከበር በርካታ በረራዎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።

አሜሪካን ኤርላየንስ 340 አውሮፕላኖቹ ሥራ በማቆማቸው በረራዎች እንደሚዘገዩ ገልጿል። የመተግበሪያ ማሻሻያዎቹ እስከ ቅዳሜ እንደሚጠናቀቁም አስታውቋል።

በአውስትራሊያ በአነስተኛ ዋጋ የበረራ አገልግሎት የሚሰጠው ጀትስታር አውሮፕላን ማረፊያ፤ 90 በረራዎች ሰርዟል።

የዩናይትድ ኪንግደም የአቪዬሽን ባለሥልጣን ቲም ጆንሰን "በቀጣይ ቀናት የተወሰኑ በረራዎች መሰረዛቸው አልያም መዘግየታቸው አይቀርም" ብለዋል።

"በአውሮፕላን መጓዝ አሁንም ቢሆን ደኅንነቱ የተጠበቀ አማራጭ ነው። አውሮፕላን ማረፊያዎች ጥንቃቄ የተሞላው ፍተሻ እና ጥገና ያደርጋሉ። በርካታ አውሮፕላኖች በአንድ ጊዜ ከበረራ የሚታገዱበት አጋጣሚ ውስን ነው" ሲሉም አክለዋል።

ኤ320 የገጠመው ችግር አውሮፕላኖች ከፍታቸውን ለማስላት የሚጠቀሙበትን መተግበሪያ ያውካል።

አውሮፕላኖቹ ከፍታን አስልተው መረጃ የሚሰጡበት መተግበሪያ በዋነኛነት በፀሐይ ጨረር ምክንያት በአግባቡ እየሠራ አይደለም።

ያለፈው ጥቅምት ላይ ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን ከፍታውን የሳተውም ለዚህ ነው። ኤርባስ እንዲህ ያለ ችግር ሲገጥመው የመጀመሪያው መሆኑን ገልጿል።

የአውሮፓ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባወጣው መመሪያ መሠረት፤ አውሮፕላኖቹ ባጠቃላይ ማሻሻያ እስከሚደረግላቸው ድረስ መብረር አይችሉም።

ደኅንነታቸው አስተማማኝ መሆኑ እስከሚረጋጥ ድረስ ተሳፋሪዎች ሳይጭኑ የሙከራ በረራ ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ኤ320 አውሮፕላኖች የበረራ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ፓይለቶች በኮምፒውተር በሚያስተላልፉት ትዕዛዝ ነው።