ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውስትራሊያው አየር መንገድ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሰራተኞቹን በህገወጥ መንገድ በማባረሩ 90 ሚሊዮን ዶላር ተቀጣ
የአውስትራሊያው ግዙፉ አየር መንገድ ኳንታስ በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ወቅት 1 ሺህ 800 የሚሆኑ ሰራተኞችን በህገወጥ መንገድ በማባረሩ 90 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ፍርድ ቤት ወሰነበት።
በአገሪቱ የተደነገገው የኢንዱስትሪ ግንኙነቶች ህጎችን በመጣስ ፍርድ ቤቱ የጣለውን ቅጣት በበጎ እንደሚያየው የአውስትራሊያ የትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር ገልጿል።
ኳንታስ በፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት ማጣቱን ተከትሎ ላባረራቸው ሰራተኞች 120 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ባለፈው ዓመት የተስማማ ሲሆን፤ ይህ ቅጣት ለሰራተኞቹ ከሚከፍለው ካሳ በተጨማሪ ነው።
ውሳኔውን ያስተላለፉት የፌደራሉ ፍርድ ቤት ዳኛ ማይክል ሊ ቅጣቱ ለሌሎች ቀጣሪዎች "ማስተማሪያ" እንደሚሆን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በበኩሉ ቅጣቱን ለመክፈል ከመስማማቱ ፤በተጨማሪም ብይኑ "ጉዳት" ለደረሰባቸው ሰራተኞች ድርጊት ተጠያቂ የሚያደርግ ነው ሲል አክሏል።
"ከ1,820 በላይ የሚሆኑ መሬት ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞቻችን እንዲሁም በዚህ ምክንያት ለተጎዱ ቤተሰቦቻቸው ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን" ሲሉ የኳንታስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቫኔሳ ሃድሰን ተናግረዋል።
"ከአምስት ዓመታት በፊት ያውም በዚያ ፈታኝ ወቅት የኩባንያችንን አገልግሎት ለሶስተኛ ወገን የመስጠት ውሳኔ በርካታ የቀድሞ ሰራተኞቻችን እና ቤተሰቦቻችን ለከፋ ችግር የዳረገ ነው" ብለዋል።
ሰራተኞች እና አሰሪዎች ሊኖራቸው የሚገቡ ግንኙነትን በሚደነግገው ፍትሃዊ የስራ አዋጅ መሰረት በአንድ የአውስትራሊያ ኩባንያ ላይ የተጣለ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ነው።
የአውስትራሊያ ትልቁ አየር መንገድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በተገታበት ወቅት መሬት ላይ ያሉ ሰራተኞችን አገልግሎት ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ማኮናተሩ መሰረታዊ የፋይናንስ እርምጃ ነው ሲል እየተከራከረ ለዓመታት ያህል በዘለቀ የፍርድ ሂደት ሲከራከር ነበር።
ፍርድ ቤቱ፤ ኳንታስ ሰራተኞቹን ከስራ በመቀነሱ ምክንያት ለከሰሰው የትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር 50 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ እንዲከፍል ብያኔ አስተላልፏል።
ውሳኔው "የዳዊትና የጎልያድ የአምስት ዓመት ፍልሚያ ማክተሚያ" እንዲሁም "በአየር መንገዱ ውስጥ ስራቸውን ይወዱ ለነበሩ ታማኝ ሰራተኞች ፍትህን የሰጠ ነው" ሲል የትራንስፖርት ማኅበሩ በመግለጫው አትቷል።
ቅጣቱ የአውስትራሊያን የስራ ቦታ ህጎች በመጣስ ከተጣሉት ከፍተኛው እንደሆነም ተገልጿል።
ዳኛ ሊ ቅጣቱ ትልልቅ ኩባንያዎች እንዲይህ አይነት ተግባራትን ፈጽመው ተጠያቂነት አይመጣብንም ለሚሉ "ማስተማሪያ" እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዳኛው በተጨማሪ የኳንታስን የተቋም ባህልን በማንሳት ኩባንያው ጸጸቱ እውነተኛ ነው ሲሉም ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸውን ከፍርድ ቤት የተገኙ ሰነዶች ያስረዳሉ።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም አዝኘላቼዋለሁ ላላቸው ሰራተኞች ምንም አይነት ካሳን ለመክፈል "የማያቋርጡ እና ጥል በተሞላበት አካሄድ" የህግ ስትራቴጂን ተከትሎ ሄዷል ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል።
ኳንታስ በአውሮፓውያኑ 2021 የሰራተኞቹን እርምጃ ለመገደብ በሚል የተወሰነውን አገልግሎቱን ለሶስተኛ ወገን ማኮናተሩን ፍርድ ቤቱ ደርሸበታለሁ ብሏል።
ከስራ ከተባረሩ መካከል አብዛኞቹ የሰራተኞች ማህበር አባላት ናቸው።