ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ የባሕር ኃይል አዛዥ የቬንዝዌላ ጀልባ ላይ በድጋሚ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዙ
የአሜሪካ ከፍተኛ የባሕር ኃይል አዛዥ፤ አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራል በተባለ የቬንዝዌላ ጀልባ ላይ በድጋሚ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ዋይት ሀውስ አስታወቀ።
በቬንዝዌላው ጀልባ ላይ እርምጃ ሲወሰድ ይሄ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮላይን ሌቪት "አድሚራል ፍራንክ ብራድሊ ሥልጣናቸውን እና ሕጉን ተከትለው ውሳኔውን አስተላልፈዋል" ብለዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ጸሐፊ ፒት ሄግዚት እንዳሉት፤ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው "ሁሉንም ሰዎች ግደሉ" አልተባለም።
ከመጀመሪያው ዙር የአሜሪካ ጥቃት የተረፉ ሁለት ሰዎች ጀልባው ላይ እንደሚገኙ ከታወቀ በኋላ ሁለተኛው ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ መሰጠቱ ተዘግቧል። ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ በሕይወት የተረፉት ሰዎች በጥቃቱ የተቃጠለው ጀልባ ላይ ተንጠልጥለው ቆይተዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የዴሞክራት እና ሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ጥቃቱን በተመለከተ በምክር ቤት ግምገማ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልት ትራምፕ እና ፒት ሄግዚት "የጦርነት ሕግን ተከትለው የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ሽብርተኞች ላይ እርምጃ ይወስዳሉ" ሲሉ የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ሁለት ሰዎች ስለመትረፋቸውም ሆነ ሁለተኛው ጥቃት በቀጥታ ሁለቱን ሰዎች ዒላማ ስለማድረጉ ማረጋገጫ አልሰጡም።
ፒት ሄግዚት በሕይወት የተረፉት ሰዎች እንዲገደሉ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የመጀመሪያው ጥቃት እአአ መስከረም 2/2025 ነበር የተፈጸመው። አሜሪካ በካሪቢያን አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራሉ ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ተነስቷል።
ሄግዚት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን "እሳት የሚያቀጣጥሉ፣ የፈጠራ እና የንቀት" ሲሉ አጣጥለዋል።
ጥቃቱ በድጋሚ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡትን አድሚራል ብራድሊ "የአሜሪካ ጀግና" ሲሉ አሞካሽተው "መስከረም ላይ የወሰደውን እርምጃም፣ አሁን ያስተላለፈውንም ውሳኔ እደግፋለሁ" ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት አሜሪካ በካሪቢያን ያላትን ወታደራዊ ኃይል አጠናክራለች። አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ጀልባዎችን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው የተባሉ ጥቃቶች በቬንዝዌላ እና ኮሎምቢያ የባሕር ይዞታዎች ላይ ተፈጽመዋል።
ካለፈው መስከረም ጀምሮ በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
አሜሪካ እግረኛ ጦር በቬንዝዌላ ልታሰማራ እንደምትችል ትራምፕ ዝተዋል። ውሳኔያቸውን የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች ተችተዋል።
የአሜሪካ ሴኔት ወታደራዊ እርምጃዎች ቋሚ ኮሚቴ "እውነታቸውን እንደሚያጣራ" አስታውቋል።
ሪፐብሊካኑ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሴናተር ሮጀር ዊከር እንዳሉት፤ ኦፕሬሽኑን ከሚመሩት አድሚራል ጋር ቃለ ምልልስ ይደረጋል። ምን ዓይነት ትዕዛዝ እንደተላለፈ ለማጣራት የድምጽ እና የምሥል ቅጂዎችም ይመረመራሉ።
የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የሚገኙበት ኮሚቴ ስለ ጥቃቱ "ዓላማ እና ሕጋዊነት" ምርመራ እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች እንደገለጹት፤ ከመጀመሪያው ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ሁለተኛ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ መሰጠቱ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ይጥሳል።
የትራምፕ አስተዳደር በካሪቢያን የከፈተው ዘመቻ ዓለም አቀፍ ውጊያ ሳይሆን፤ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ዒላማ ያደረገ መሆኑን ደጋግሞ ገልጿል።
በጄኔቫ ስምምነት መሠረት በጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ ሕገ ወጥ ሲሆን፤ ለተጎጂዎቹ ሕክምና መስጠትም ግዴታ ነው።
ቬንዝዌላ በጀልባው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዛለች። "ጥልቅ ምርመራ" እንደሚደረግም አስታውቃለች።
አሜሪካ ጥቃት በመፈጸም ቀጣናውን እያወከች ነው ስትል ቬንዝዌላ ከስሳለች። የትራምፕ አስተዳደር ግብ የቬንዝዌላን መንግሥት ማውደር እንደሆነም ገልጻለች።