ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቬንዙዌላ ትራምፕ የአየር ክልሏን ለመዝጋት ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ 'የቅኝ ገዢዎች ማስፈራሪያ' ስትል ገለጸች
ቬንዙዌላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ዙሪያ ያለው የአየር ክልል ዝግ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ "የቅኝ ገዢዎች ማስፈራሪያን" እየተጠቀሙ ነው ስትል ከሰሰች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የትራምፕን አስተያየቶች "በቬንዙዌላ ሕዝብ ላይ ሌላ ከልክ ያለፈ፣ ሕገወጥ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቃት" ሲሉ ጠርተውታል።
አሜሪካ የሌላ አገርን የአየር ክልል በሕጋዊ መንገድ የመዝጋት ሥልጣን የላትም፤ የትራምፕ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ የጉዞ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እና አየር መንገዶች በአካባቢው እንዳይንቀሳቀሱ ሊያግድ ይችላል።
አሜሪካ ወታደሮቿን የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመዋጋት በሚል ወደ ካሪቢያን ባሕር አስጠግታለች።
የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የአሜሪካን የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ለመግታት የሚል ምክንያት ውድቅ አድርገውታል።
ከዚያ ይልቅ አሜሪካ ጦሯን እያስጠጋች ያለችው እርሳቸውን ከሥልጣን ለማስወገድ የሚደረግ ሙከራ ነው ብለዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ "ለሁሉም አየር መንገዶች፣ አብራሪዎች፣ ለዕፅ እና ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች፣ በቬንዙዌላ እና አካባቢው ያለው የአየር ክልል በሙሉ ስለሚዘጋ ጥንቃቄ አድርጉ" ሲሉ ጽፈዋል።
ዋይት ሐውስ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።
ትራምፕ ዛቻውን እያጠናከሩ ሲሄዱ፣ የዴሞክራት እና የሪፐብሊካን የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ፕሬዚዳንቱ የሕግ አውጪውን ይሁንታ ባለማግኘታቸው ቁጣቸውን ገልጸዋል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቬንዙዌላ ላይ የፈጸሟቸው ግድ የለሽ ድርጊቶች አሜሪካን ወደ ሌላ ውድ የሆነ የውጭ ጦርነት እየገፉ ነው" ሲሉ ዴሞክራቱ ሴኔት ቻክ ሹመር እሁድ ዕለት በ'ኤክስ' ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
"በሕገ መንግሥታችን መሠረት፤ ጦርነት የማወጅ ብቸኛ ሥልጣን ያለው ኮንግረሱ ነው" ሲሉም አክለዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትራምፕ አጋር የነበሩት የሪፐብሊካን ተወካይ ማርጆሪ ቴይለር ግሪን "ጦርነት የማወጅ ብቸኛ ሥልጣን የኮንግረስ ነው" ብለዋል።
የትራምፕ አስተያየቶች የተሰጡት የአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (FAA) አየር መንገዶችን "በቬንዙዌላ እና አካባቢዋ የጨመረውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ" በተመለከተ ካስጠነቀቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የቬንዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ ወደ ቬንዙዌላ የምትመልሳቸውን ስደተኞችን የያዙ በረራዎችን "በአንድ ወገን" ማስቆሙን ተናግሯል።
"በቀጥታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የዓለም ሉዓላዊ መንግሥታት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሚመለከታቸው ባለብዙ ወገን ድርጅቶች ይህንን ኢ-ሞራላዊ የጥቃት ተግባር በጥብቅ እንዲቃወሙ ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።
እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት የቬንዙዌላ ጦር በባህር ዳርቻ አካባቢዎች ልምምዶችን አካሂዷል። የመንግሥት ቴሌቪዥን የአየር መቃወሚያዎች፣ የጦር መሳሪያዎች እና ሌሎች መድፎች ወደ ስፍራው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አሳይቷል።
አሜሪካ በዓለም ላይ ትልቁን የጦር መርከብ (USS Gerald R Ford) ወደ 15,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ከቬንዙዌላ በቅርብ ርቀት ላይ አሰማርታለች።
አሜሪካ እአአ በ1989 ፓናማን ከወረረች ወዲህ በአካባቢው ያደረገችው ግዙፍ ወታደራዊ ስምሪት ሲሆን ሰበቡም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመዋጋት እንደሆነ በተደጋጋሚ ትናገራለች።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት የቬንዙዌላ የዕፅ ዝውውርን ለመግታት "በመሬት" የሚደረጉ የአሜሪካ ጥረቶች "በቅርቡ" እንደሚጀምሩ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ኃይሎች አደንዛዥ ዕጾችን እንደያዙ በተናገሩት ጀልባዎች ላይ ቢያንስ 21 ጥቃቶችን ፈጽመዋል፤ ይህም ከ80 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ሆኖም አሜሪካ ጀልባዎቹ አደንዛዥ ዕጾችን እንደያዙ የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረበም።
የቬንዙዌላ መንግሥት የአሜሪካ እርምጃ ዓላማ ባለፈው ዓመት በቬንዙዌላ ተቃዋሚዎች እና በብዙ የውጭ አገራት ተጨበርብሯል የተባለውን ምርጫ ያሸነፉትን ማዱሮን ከሥልጣን ማስወገድ እንደሆነ ያምናል።