ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ጦር በጋዛ እርዳታ እየተጠባበቁ የነበሩ 67 ፍልስጤማውያንን መግደሉ ተገለጸ
የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ መኪናዎችን እየተጠባባቁ የነበሩ ቢያንስ 67 ፍልስጤማውያንን መግደሉን በሐማስ የሚመራው የግዛቲቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ 25 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ስፍራው ሲደርሱ "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተራቡ ፍልስጤማውያን" ተኩስ ተከፍቶባቸዋል ብሏል።
ተሽከርካሪዎቹ የእስራኤልን ድንበር አቋርጠው የፍተሻ ኬላዎችን አልፈው ወደ ጋዛ እንደደረሱ ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (አይዲኤፍ) "አፋጣኝ ስጋት" ያለውን ለማስወገድ "የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን መተኮሱን ገልጿል። ሆኖም የተገደሉ ሰዎችን አኃዝ አልተቀበለም።
የጤና ሚኒስቴሩ በጋዛ ያለው ረሃብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እና በርካቶች ወደ ተቋሙ የሚመጡ ፍልስጤማውያን ምግብ ከማጣታቸው የተነሳ "በከፍተኛ ድካም ዝለው" እንደሆነ ቅዳሜ ዕለት አስጠንቅቋል።
"በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በረሃብ የተነሳ ሊሞቱ አፈፋ ላይ ናቸው" ሲል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ለረሃብ እንደተጋለጡ እና መሰረታዊ ሸቀጦች ወደ ስፍራው በአፋጣኝ እንዲገቡ ጠይቋል።
በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሰዎች "በረሃብ ምክንያት" መሞታቸውን እሁድ ዕለት ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ በርካቶች በሰሜናዊ ጋዛ ወደሚገኘው ሺፋ ሆስፒታል እየተወሰዱ ነው።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሐሰን አል ሻየር ለቢቢሲ አረብኛ እንደተነገሩት የጤና ማዕከሉ "በከፍተኛ ሁኔታ መጨናቁን" ነው።
ከሆስፒታሉ ውጭ የነበረች አንዲት ሴት "መላው ህዝብ በረሃብ እየረገፈ ነው" ስትል ለቢቢሲ አረብኛ ተናግራለች።
"ልጆች የሚቀመስ ስሌላቸው በረሃብ እየሞቱ ነው። በርካቶች ህይወታቸውን ለማቆየት ውሃ በጨው እየጠጡ ነው፤ ጨውና ውሃ ብቻ" ስትል ያለውን አስከፊ ሁኔታ ገልጻለች።
በረሃብ ከሞቱት በተጨማሪ የእስራኤል ጦር እርዳታ እየተጠባበቁ በነበሩ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 93 መድረሱን እና በርካቶች ደግሞ መቁሰላቸውን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ገልጿል።
በሰሜናዊ ጋዛ 80 ሰዎች ሲገደሉ፤ በደቡባዊ ጋዛ ደግሞ በራፋህ በሚገኝ የእርዳታ ጣቢያ አቅራቢያ ዘጠኝ ፍልስጤማውያን እንዲሁም በኻን ዩኒስ እርዳታ ጣቢያ አቅራቢያ እንዲሁም አራት ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ኤጀንሲው አክሏል።
በጋዛ ከተማ ቃሴም አቡ ካተር ዱቄት ለመቀበል ባመራበት ወቅት በርካታ ፍልስጤማውያን ምግብ ለማግኘት "እየተገፋፉ" እንደነበር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።
"የእስራኤል ታንኮች ተኩስ ከፈቱብን። የእስራኤል አልሞ ተኮሻች ደግሞ እንስሳትን በጫካ ውስጥ እያደኑ ይመስል በህዝቡ ላይ ይተኩሱበት ነበር" ብሏል።
"በርካቶች ዓይኔ እያየ በተከፈተባቸው ተኩስ ረገፉ፤ ማንም ህይወታቸውን ሊታደገው አልቻለም" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ፕሮግራም ድርጅት ዕርዳታ እየተጠባበቁ እየነበሩ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸም "ፍጹም ተቀባይነት የለውም" ሲል አውግዟል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ተቋም አቋቁመዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
እስካሁን ድረስ የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ 798 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አርብ ዕለት አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 615 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ፋውንዴሽኑን የሚያስተዳድረው የአሜሪካ የግል የጥበቃ ቡድን ሲሆኑ ማዕከላቱ የሚገኙትም በደቡብ እና መከካከለኛው ጋዛ ወታደራዊ ቀጣናዎች ውስጥ ነው።
ሌሎች 183 ግድያዎች ደግሞ የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።