የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት መንገድ ላይ ከተጎነተሉ በኋላ ክስ ሊመሰርቱ ነው

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡአም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡአም በሕዝባዊ መርሀ ግብር ላይ ጉንተላ ያደረሰባቸው ግለሰብ ላይ ክስ ሊመሰርቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት ይፋ የሆነ በስልክ የተቀረፀ ተንቀሳቃሽ ምስል በሜክሲኮ ከተማ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ባለ መንገድ ላይ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ሲነጋገሩ ያሳያል።

በምስሉ ላይ አንድ ወንድ ከኋላቸው ጠጋ በማለት አንገታቸው ስር ለመሳም ሲሞክር እና ገላቸውን በእጆቹ ሲነካ ታይቷል።

ፕሬዝዳንቷ በፍጥነት ሲንቀሳቀሱ እና የቡድናቸው አባል በመሀል ሀብቶ ሁኔታው የረገበ ቢሆንም በድርጊቱ ተደናግጠዋል።

ጥቃቱ አድራሹ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።

"አቤቱታ የማላስገባ ከሆነ ሌሎች ሜክሲኳዊ ሴቶች ምን ይሆናሉ? ፕሬዝዳንታቸው ላይ እንደዚህ ካደረጉ በአገሪቱ ሁሉም ሴቶች ላይ ምን ሊፈጠር ይችላል?" ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

"ክስ ለመመስረት የወሰንኩበት ምክንያት በሴትነቴ የገጠመኝ በመሆኑ ነው፤ የዚህ አገር ሴቶች የሚገጥማቸው ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ "ከዚህ ቀደምም ፕሬዝዳንት ከመሆኔ በፊት ተማሪ እያለሁ ደርሶብኛል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡአም ተጠርጣሪው ላይ ክስ ለመመስረት የወሰኑት ግለሰቡ በሁነቱ ላይ የነበሩ ሌሎች ሴቶች ላይም ትንኮሳ በመፈፀሙ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

"መስመሩ መሰመር አለበት" ብለዋል።

የሴቶች መብት ቡድኖቶች እና የሴታዊት መብት አቀንቃኞች ፕሬዝዳንቷ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሜክሲኮ ማኅበረሰሰብ ውስጥ መርዛማ ወንዳ ወንድነት ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን ያሳያል ያሉ ሲሆን፤ ባህሪው አንድ ወንድ ፕሬዝዳንቷ ሴት ብትሆንም የትኛዋንም ሴት በኃይል የማግኘት መብት አለኝ ብሎ ሲያምን ነው።

በሜክሲኮ የሴቶች ግድያም ከፍተኛ ሲሆን፤ 98 በመቶ የሚሆን ፆታዊ ጥቃት ግድያዎች ያለቅጣት እንደሚቀሩ ይገመታል።

ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡአም እጩ ሆነው ሲወዳደሩ ጉዳዩን ለመቀልበስ ቃል የገቡ ቢሆንም አስተዳደራቸው እስካሁን የሴቶችን ግድያ አይነት ከባድ ወንጀሎችን ለመቀነስ እምብዛም ማሻሻል አልቻለም።

የፕሬዝዳንቷ የጥቃት ክስተት የመጣው በሜክሲኮ አካላዊ ደኅንነት እና በሰፊው የፖለቲከኞች ደኅንነት የውይይት ርዕስ በሆነበት ጊዜ ነው።

ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሽንቡአም የተኳቸውን ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማንኤል ሎፔዝ ኦብራዶን ፈለግ በመከተል ከተጋፊዎቻቸው ጋር ጎዳናዎች እና በሁለቶች ላይ መደበኛ እና የቅርብ ግንኙነት አላቸው።

እንቅስቃሴያቸው አልፎ አልፎ የደኅንነት ችግር የገጠመው ቢሆንም ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ ጥቃቱን ተከትሎ ፖሊሲያቸውን እንደማይለውጡ ተናግረዋል።