ሊደፍራት የሞከረን ግለሰብ ምላስ በመንከሷ ጥፋተኛ የተባለችው ደቡብ ኮርያዊት ይቅርታ ተጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በደቡብ ኮሪያ ከ60 ዓመታት በፊት በደረሰባት የፆታዊ ጥቃት ራሷን በመከላከሏ ጥፋተኛ የተባለችውን ግለሰብ አቃቤ ሕግ ይቅርታ ጠየቀ።
ቾይ ማል ጃ እአአ በ1964 የ18 ዓመት ልጅ ሳለለች ሊደፍራት የሚከረን ግለሰብ ምላስ በከፊል በመንከሷ የ10 ወራት እስር እና የሁለት ዓመት እግድ ተፈርዶባት ነበር።
የ78 ዓመቷ ቾይ በአገሪቷ ሚ ቱ (#MeToo) እንቅስቃሴ በመነሳሳት በወቅቱ የተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግላት ለዓመታት ዘመቻ ስታደርግ ቆይታለች።
ዳግም ጉዳይዋ መታየት የጀመረው ረብዑ ዕለት በቡሳን ከተማ ሲሆን አቃብያነ ሕጎች ይቅርታ ጠይቀው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔዋን እንዲሰርዝ አመልክተዋል።
ከችሎቱ በፊት ከፍርድ ቤት ውጪ ለተሰባሰቡት ጋዜጠኞች ቾይ "ለ61 ዓመታት መንግሥት እንደ ወንጀለኛ እንድኖር አድርጎኛል" ስትል ተናግራ ነበር።
መጪው ትውልድ ከፆታዊ ጥቃት የፀዳ ደስተኛ ሕይወት እንዲኖር ምኞቷ መሆኑንም ተናግራለች።
በፍርድ ሂደቱ መጀመሪያ ላይ የቡሳን ዋና አቃቤ ሕግ ጄኦንግ ሚዮንግ ዎን "ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።
"ራሷን ብቻዋን ከወሲብ ጥቃት መከላከል የነበረባትን ተጠቂ ቾይ ማል ጃን በቃላት ሊገለጽ ለማይችል ስቃይ እና ሕመም ዳርገናታል።"
የመጨረሻ ብይን ለመስከረም 10 ተቀጥሯል።
የሕግ ባለሙያዎች በዕለቱ ፍርድ ቤቱ የቾይን የጥፋተኝነት ውሳኔ ይሽራል ብለው ይጠብቃሉ።
ከችሎቱ ውጪ ቾይ እጇንን ከፍ አድርጋ "አሸነፍን!" በማለት እሷን ለመደገፍ ለተሰበሰቡ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተናግራለች።
እአአ በ1964 18 ዓመቷ የነበረው ቾይ ማል ጃ በአንድ የ21 ዓመት ወጣት ጥቃት የደረሰባት በደቡብ ጂምሃ ከተማ ነው።
አጥቂው መሬት ላይ ከጣላት በኋላ ምላሱን አስገድዶ ወደ አፏ ማስገባቱን የፍርድ ቤቱ መዝገብ ያስረዳል።
1.5 ሴሜ የምትረዝመው ቾይ የአጥቂውን ምላስ በመንከስ ከጥቃቱ አምልጣለች።
አጥቂው የግለሰብን መብት በመተላለፍ እና በማስፈራራት የስድስት ወር እስራት እንዲሁም የሁለት ዓመት እግድ ተፈርዶበታል።
በአስገድዶ መድፈር ሙከራ ወንጀል አልተከሰሰም።
ቾይ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረሷ ከአጥቂዋ የበለጠ ቅጣት ተጥሎባታል።
ፍርድ ቤቱ በወቅቱ ድርጊቱ ራሷን ከመከላከል "ምክንያታዊ ወሰን" አልፏል ብሎ ነበር።
የቾይ የፍርድ ውሳኔ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ በሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ፍርድ ቤት በወሲባዊ ጥቃት ወቅት ራስን መከላከልን እውቅና አለመስጠቱን ለማስተማር እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።
"በዚህች አገር ፍትህ ህያው ነው"
እአአ በ2010ቹ መገባደጃ ላይ የደቡብ ኮሪያ የሚ ቱ (#MeToo) እንቅስቃሴ መነሻ ያደረገችው ቾይ ጉዳይዋ በድጋሚ በፍርድ ቤት እንዲታይላት ጥያቄ ለማቅረብ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች ጋር መስራት ጀምራለች።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከ56 ዓመታት በኋላ በ2020 አቤቱታ ብታቀርብም መጀመሪያ ላይ በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ተደርጓል።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቾይ ዳግም የክስ ሂደቷ ሊቀጥል እንደሚችል ወስኗል።
ለፍትህ የምታደርገው ትግል በደቡብ ኮሪያ ዝነኛ እየሆነ የመጣው ቾይ፣ ከመብት ተሟጋቾች ጋር በመሆን በሴኡል በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂዳለች።
ረቡዕ ዕለት ከችሎት በኋላ "እስካሁን ማመን አልቻልኩም" ማለቷን የኮሪያ ጁንግአንግ ዴይሊ ጋዜጣ ዘግቧል።
"አቃቤ ሕግ ስህተቱን እያመነ ከሆነ ግን በዚህች አገር ፍትህ ህያው ነው ብዬ አምናለሁ" ስትል አክላለች።















