የኖርዌይ ልዕልት ልጅ አራት የመድፈር ወንጀሎችን ጨምሮ በርካታ ክሶች ተመሰረቱበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኖርዌይ የዘውዳዊ ልዕልት የመጀመሪያ ልጅ አራት የመድፈር ድርጊቶችን ጨምሮ በ32 ወንጀሎች ክስ እንደተመሰረተበት የሀገሪቱ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
የ28 ዓመቱ ማሪየስ ቦርግ ሄቢ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል በቀድሞ ፍቅረኛው ላይ በደል መፈፀም እና በሌላ የቀድሞ ፍቅረኛው ላይ የተሰጡትን የእግድ ትዕዛዞች መጣስ የሚሉት ይገኙበታል።
የወደፊቱ የኖርዌይ ንጉስ እንደሚሆን የሚጠበቀው ልዑል ሃኮን ሚስት የሆነችው ልዕልት ሜቴ ማሪት ልጅ የሆነው ቦርግ ሄቢ፤ ልዕልቷ ከዚህ ቀደም በነበራት ግንኙነት የተወለደ ነው።
ሆቢ ከቀረቡበት ክሶች ውስጥ ከባድ በሆኑት ላይ የሚቀርብበትን ውንጀላ ክዶ የሚከራከር ሲሆን አንዳንድ አነስተኛ ክሶችን በተመለከተ ግን የፍርድ ሂደቱ ሲጀመር ጥፋተኛነቱን እንደሚቀበል ጠበቃው ፔታር ሴኩሊች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በቀረቡበት ከፍተኛ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ የበርካታ ሴቶችን ሀፍረተ ስጋ እነርሱ ሳያውቁ ወይም ፈቃድ ሳይሰጡት በመቅረጽ ወንጀልም ክስ እንደተመሰረተበት ዐቃቤ ህግ ስቱርላ ሄንሪክስቦ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ጠበቃው በበኩላቸው "መድፈር እና የቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት የቀረቡበትን ክሶች አይቀበልም" ሲሉ የደንበኛቸውን አቋም እንደገለጹ ሮይተርስ ዘግቧል።
የኖርዌይ ልዑል ሃኮን በእንጀራ ልጃቸው ላይ ስለቀረቡት ክሶች ማክሰኞ ዕለት በተናገሩበት ሰዓት፤ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው የሚወሰነው በፍርድ ቤቶች መሆኑን ገልጸዋል።
ሁኔታው በክስ ሂደቱ ውስጥ ለሚሳተፉ ሰዎች በሙሉ "እጅግ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ሆኖ" ሊሆን እንደሚችልም መናገራቸውን የኖርዌይ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የሆነው ኤንአርኬ ዘግቧል።
በሄቦ ክስ ላይ የተካተቱት አራት የመድፈር ወንጀሎች ከ2018 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ እንደተከሰቱ እንዲሁም ከእነዚህ ውስጥም አንዱ ከታሰረ በኋላ የተፈጸመ እንደሆነም ዘገባው ያመለክታል።
የንጉሳዊ ማዕረግ ወይም ኦፊሴላዊ ኃላፊነቶች የሌሉት ሄቢ፤ በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2024 ነሀሴ፣ መስከረም እና ህዳር ላይ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ለእስር ተዳርጎ ነበር።
ነሀሴ ላይ በቁጥጥር ስር ከዋለ ጊዜ አንስቶ የጥቃት ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደበት ነው።
ሰኔ ወር ላይ ደግሞ በሶስት የመድፈር እና በ23 ሌሎች ወንጀሎች እንደተጠረጠረ ፖሊስ አስታውቋል።
የልዕልቷ ልጅ የፍርድ ሂደት በሚቀጥለው ዓመት ጥር ወር ላይ ሊጀመር እንደሚችል እና ስድስት ሳምንታት ገደማ ሊቆይ እንደሚችል ዐቃቤ ህግ ገልጿል።















