ኮንጎ መፈንቅለ መንግሥት አልተፈጸመም በማለት ሕዝቡ እንዲረጋጋ አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮንጎ ብራዛቪል በፕሬዝዳንት ዴኒስ ኑጌሶ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሟል የተባለው ሐሰት ነው ተባለ።
የአገሪቱ መንግሥት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሟል እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰተኛ ነው ያለ ሲሆን ዜጎች በተረጋጋ መንፈስ ወደ ዕለታዊ ሕይወታቸው እንዲያመሩ አሳስቧል።
ቀደም ሲል ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች የአገሪቱ ጦር ሠራዊት የአገሪቱ መሪ ለሥራ ከአገር መውጣታቸውን ጠብቀው መፈንቅለ መንግሥት ፈጽመዋል የሚሉ ነበሩ።
ይሁን እንጂ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢንፎርሜሽን ሚንስትር መፈንቅለ መንግሥት የመፈጸሙ ዜና ሐሰተኛ ነው ብለዋል።
ኮንጎ ብራዛቪልን ለ39 ዓመታት የመሩት የ79 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ኑጌሶ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ ይገኛሉ።
የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ሕዝቡ እንዲረጋጋ እና ወደ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው እንዲመለስ እናሳስባለን ብለዋል።
የአገሪቱ መንግሥትም በተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግሥቱ መፈጸም ዜና ሐሰተኛ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በቅርቡ በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መፈንቅለ መንግሥቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።
የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበሩት ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና በቅርቡ ደግሞ በጋቦን መፈንቅለ መንግሥታት መካሄዱ ይታወሳል።
ፕሬዝዳብት ዴኒስ ኑጌሶ በነዳጅ ሃብት የበለጸገችውን አፍሪካዊት አገር መምራት የጀመሩት እአአ 1979 ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከመሩ በኋላ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያው የኮንጎ መድበለ ፓርቲ ምርጫ እአአ 1992 ላይ ቢሸነፉም በአገሪቱ ከተካሄደ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ እአአ 1997 ዳግም ወደ ስልጣን ተመልሰዋል።
የኮንጎ ብራዛቪሉ ፕሬዝዳንት ለረዥም ዓመታት ስልጣን ላይ ከቆዩ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
የኢኳቶቲያል ጊኒው መሪ ቴኦዶር ኦቢያን ከእአአ 1979 ጀምሮ አገሪቱን ለ44 ዓመታት በመምራት ስልጣን ላይ ለረዥም ዓመታት የቆዩ የአገሪ መሪ ሲሆኑ የካሜሮኑ ፓል ቢያ ደግሞ የመካከለኛዋን አፍሪካ አገር ለ40ኛ ተከታታይ ዓመታት በመምራት ላይ ይገኛሉ።












