ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናን የኤድስ ወረርሽኝ ያጋለጡት ዶክተር በ95 ዓመታቸው አረፉ
በገጠራማዋ ቻይና የነበረውን የኤድስ ወረርሽኝ ያጋለጡት እና ለግዞት የተዳረጉት ቻይናዊቷ ዶክተር ጋኦ ያኦጄ በ95 ዓመታቸው አረፉ።
ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ለስደት የተዳረጉት ዶክተር ጋኦ በኒውዮርክ ህይወታቸው ማለፉን ጓደኛቸው አስታውቀዋል።
በአገሪቷ በነበረው ደም ሽያጭ ምክንያት የበርካታ ገጠር መንደሮች በኤችአይቪ ቫይረስ መበከላቸውንም ይፋ አድርገዋል።
በቻይና የኤድስን ወረርሽኝን በመከላከል ግንባር ቀደም ታጋይ የነበሩት ዶክተሯ ህሙማንንም ለማከም በራሳቸው ወጪ በርካታ ጉዞዎችን አድርገዋል።
በሻንዶንግ ግዛት በአውሮፓውያኑ 1927 የተወለዱት ዶ/ር ጋኦ የማህጸን ሐኪም ናቸው ሲሆኑ የመጀመሪያ የኤድስ ታማሚም ያገኙት በአውሮፓውያኑ 1996 በማዕከላዊ ሄናን ግዛት ነው።
ዶክተር ጋኦ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ ይኖሩበት በነበረው እንደ ሄናን ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ደም መሸጥ የተለመደ ነበር። አርሶ አደሩ ማህበረሰብ በነበረው የምጣኔ ኃብት እድል አናሳነት ኑሯቸውን ለመግፋት ከባድ ስላደገረውም ደም መሸጥን እንደ አማራጭ ገንዘብ ማግኛ ነበር ያዩት። የአካባቢው ባለስልጣናትም ይህንኑ ይደግፉት ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ በቻይና ገጠራማ አካባቢ የኤችአይቪ ምርመራ አነስተኛ መሆኑ፣ ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅኛ ከመሆኑ ጋርም ተያይዞ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሰዎች ደም እንዲወሰድ እና ለበሽታው መዛመትም ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
በዚያን ጊዜ የቻይና ባለስልጣናት ኤችአይ ቪ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ወሲባዊ ግንኙነት እና ከእናት ወደ ልጅ እንደሆነም ነው ይናገሩ የነበሩት።
ዶክተሯ በመጀመሪያ ያገኟት ታማሚ ባለቤቷም ሆነ ልጇ በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ የሌለባቸው ሲሆን ታማሚዋ ቫይረሱ የተላለፈባት ከደም ልገሳ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገነዘቡ።
ዶክተር ጋኦ ሁኔታውንም ለመረዳት የሄናን መንደሮችን መጎብኘት ጀመሩ። ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመተባቸውን 100 መንደሮችን ጎብኝተው ከ1 ሺህ በላይ በደም ልገሳ ምክንያት የተበከሉ ቤተሰቦችን ማግኘታቸው ተዘግቧል።
በሚጓዙባቸው መንገደሮች በራሳቸው ወጪ የታተሙ ጽሁፎችን፣ ምግብ እና ልብስ ለነዋሪዎች ይሰጣሉ።
የሔናን ባለስልጣናት መጀመሪያ ላይ ድርጊቱን ለመሸፋፈን ቢሞክሩም በ1990ዎቸ አጋማሽ ደም የመሸጥ ንግድ እንዲቋረጥ አድርገዋል።
ሆኖም ዶክተር ጋኦ የደም ሽያጩ በአገሪቱ ውስጥ ያስከተለውን እና ስለቀጠለው መዘዝ መናገራቸውን ቀጠሉ። በቻይና 10 ሚሊዮን ነዋሪዎች ኤችአይቪ በደማቸው እንዳለ ይናገሩ የነበረ ሲሆን የቻይና መንግሥት በበኩሉ ይፋ ያደረገው አኃዝ 740 ሺህ ነው።
በቻይና የነበረውን የኤድስ ወረርሽኝ ያጋለጡት የመጀመሪያ ዶክተር ባይሆኑም በጥረታቸው ግን ጉዳዩ በመላው አገሪቱ እና በውጭ አገራትም እንዲታወቅ አድርገዋል።