በኬንያ መነጋገሪያ የሆነው ‘’ሐሳዊው ጠበቃ’’ አድናቂዎቹን አመሰገነ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በኬንያ ዘለግ ላሉ ዓመታት ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ለተከሳሾች ጥብቅና ሲቆም ነበር የተባለው ግለሰብ አድናቂዎቹን አመሰገነ።
ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቡ ብራይን ምዌንዳ በሚል ስም የሚታወቅ ቢሆንም ግለሰቡ ግን ማንነቱ ሌላ ነው። ይህን ስም የሚጠቀም ሌላ ሕጋዊ ጠበቃን ማንነቱ ተላብሶ ነው ግለሰቡ ለዚህ ሁሉ ጊዜ በጥብቅና የሠራው ብሏል።
ይህ ሐሳዊ የተባለው ወጣት ግን ትክክለኛው ብራየን ምዌንዳ እኔ ነኝ በሚል ነው ፍርድ ቤት በጥብቅና ሲሠራ ነው የኖረው።
የኬንያ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆን ይህ ‘’ሐሳዊ ጠበቃ’’ የሚባለው ወጣት በርካታ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ከማሸነፉም በላይ እሳት የላሰ ጠበቃ ነበር።
በተደጋጋሚ የተለያዩ ጉዳዮችን በመያዝ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሟግቶ ሲያሸንፍ የነበረው ታዲያ አንድም የሕግ ትምህርት ሳይቀስም በግል ንባብ ብቻ በመታገዝ ነው ተብሏል።
ይህ ክስተት በኬንያዊያን ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ግለሰቡ ለፈጸመው ድፍረት የተሞላበት ድርጊት በማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ድጋፍ ያሳዩ ብዙዎች ናቸው።
የኬንያ የሕግ ሶሳይቲ እና የኬንያ አቃቢ ሕግ የግለሰቡን ድርጊት ቢያወግዙም ብዙ ዜጎች ግን ግለሰቡ ሊበረታታ ነው የሚገባው ሲሉ ድጋፋቸውን ሰጥተውታል።
ይህን ተከትሎም ነው ‘’ሐሳዊው ጠበቃ’’ ለወዳጆቹ ‘’ክብረት ይስጥልኝ’’ በሚል ለአድናቂዎቹ ምስጋና ያቀረበው።
የኬንያ የንግድና ሸማቾች ማኅበር ‘’ብልህ እና ብሩህ አእምሮ ያለው ወጣት’’ ሲል ‘’ሐሳዊውን ጠበቃ’’ በአደባባይ አሞካሽቶታል።
የቀድሞው የናይሮቢ ገዥ ማይክ ሶንኮ ሐሰተኛ ነው የተባለውን ጠበቃ የኔ ጀግና ብለውታል።
ማይክ ሶንኮ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባጋሩት አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ሐሰተኛ የተባለው ወጣት ጠበቃ ከጎናቸው አብሯቸው የነበረ ሲሆን በዚህ ቪዲዮም ‘’ከጎኔ ለቆማችሁ ሁሉ አመሰግናለሁ። በጊዜ ሂደት የተፈጠረውን ውዝግብ መልክ አሲዛለሁ፤ ታገሱኝ’’ ሲል ቃል ገብቷል።
ሐሰተኛ ነው የተባለው ይህ ጠበቃ ‘’ምን እንደተፈጠረ በደንብ አስረዳለሁ፤ ስሜንም አጸዳለሁ’’ የሚል መልእክት ለአድናቂዎቹ አስተላልፏል።
ሐሰተኛው ጠበቃ በሚል እየተሞካሸ ያለው ግለሰብ ዛሬ ወይም ነገ ማክሰኞ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚሄድ ተናግሯል።
አጋርነታቸውን ለዚህ ጠበቃ የገለጹት የቀድሞው የናይሮቢ ገዥ ማይክ ሶንኮ ‘’ጠበቃው ሰው አልገደለም፤ ሰው አላስገደለም። ሽብርተኛ አይደለ፤ ምን ይሁን ነው የምትሉት?’’ ሲል ከጎኑ እንደሚቆሙ ቃል ገብቷል።
የቀድሞ የናይሮቢ ገዥ ማይክ ሶንኮ ራሳቸው በአደገኛ እጽ ዝውውር እና ገንዘብ በመሰወር ተደራራቢ ክስ አለባቸው።
ኬንያዊያን በስፋት ለዚህ ሐሰተኛ ለተባለው ወጣት ጠበቃ ድጋፋቸውን ቢገልጹም የኬንያ አቃቢ ሕግ ግን ግለሰቡ ሕግ ፊት እንደሚቀርብ አረጋግጧል።












