ለኦሊምፒክ 75 ሺህ ወታደሮችን ያሰማራችው ፓሪስ

ሜክሲኳዊቷን ቱሪስት ጨምሮ በርካቶች ፓሪስ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች አቅራቢያ ተሰባስበዋል።

ዝነኛውን ሲን ወንዝ፣ ኖተር ዳም ካቴድራል እና ሌሎችም የቱሪስት መስህቦችን ለማየት ጓጉተዋል።

ሆኖም የቱሪስት መዳረሻዎቹ እንደቀድሞው ክፍት አይደሉም። ቱሪስቶቹ በዚህ ተበሳጭተዋል።

ወደ ሲን ወንዝ ለመጓዝ የኪውአር ኮድ ሲጠየቁ ሜክሲኳዊቷ ቱሪስት በቁጣ “ኮድ የለንም” ስትል መልሳለች።

እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች በፖሊስ በተጠንቀቅ እየተጠበቁ ነው።

አይፍል ታወር አቅራቢያ ያለ ፖሊስ የእግረኞች መንገድ ዝግ ስለሆነ ጥንዶች በሌላ መንገድ እንዲሄዱ ነገራቸው።

ይሄ ሁሉ ሽር ጉድ የፓሪስ ኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ዝግጅት አካል ነው።

በመክፈቻው ቀን አትሌቶች የፓሪስን ሲን ወንዝ አልፈው ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል።

የፓሪስ ፖሊሶች እና ወታደሮች ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በደስታ ታጅበው “ዝግጁ ነን” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለሳምንታት በፖለቲካ ማዕበል ቢናጡም የወትሮው ፈገግታቸው አልጠፋም።

ለኦሊምፒክ የተሰማሩት ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና ጠባቂዎች በአጠቃላይ ወደ 75 ሺህ ይጠጋሉ።

በፈረንሳይ ታሪክ ጦርነት ሳይኖር ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ሲሰማራ ይህ የመጀመሪያው ነው።

መንገዶች እና የባቡር ሀዲዶች ተዘግተዋል። ወደ 44 ሺህ የብረት አጥሮች ቆመዋል።

ወደ ሲን ወንዝ ወይም በአቅራቢያው ያሉ ደሴቶች መጓዝ የሚፈልጉ ቱሪስቶች በኪውአር ኮር ነው ማለፍ የሚችሉት።

ሁሌም ለቱሪስቶች ክፍት የሆነችው ፓሪስ ከድሮው በተለየ መንገዶቿን ዘግታለች።

ኦማር ቤንአብደላ የተባለው የ25 ዓመት አስተናጋጅ “አካባቢው እንዲህ ፀጥ ብሎ አይቼው አላውቅም። ትንሽ ያስጨንቃል። ዘጠና በመቶ ደንበኞቻችን የሉም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የብረት አጥሮች ከኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት በኋላ ይነሱ እና ነገሮች ወደ ቀደመ መልካቸው ይመለሳሉ።

በፓሪስ የተሰማሩት 5,500 ወታደሮች የበላይ አዛዥ ጄኔራል ሊዮኔል ካርተር “ሁኔታው ያን ያህል የከፋ ነው ብዬ አላስብም። ቁርጠኛ ሆነን በትኩረት እየሠራን ነው” ይላሉ።

የኦሊምፒክ እና የፓራሊምፒክ ዝግጅት ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል እንደተመደበለት ይስማማሉ።

ከዚህ ቀደም በእስላማዊ ታጣቂዎች የደረሱ ጥቃቶችን ተከትሎ ፈረንሳይ ‘ኦፕሬሽን ሴንቲኔል’ የሚል ኦፕሬሽን ጀምራለች። የኦሊምፒክ ዝግጅትም የዚህ አካል ነው።

“ፈንጂ አምካኝ ቡድኖች፣ የአነፍናፊ ውሻ ቡድኖች፣ ፀረ ድሮን ቡድኖች አሉን። የሲን ወንዝ ተቆጣጣሪ ኃይልም አለን” ይላሉ ጄኔራሉ።

የአውሮፓውያኑ 2012 የለንደን ኦሊምፒክን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ በሰጠው ምክር መሠረት ፈረንሳይ የወታደራዊ ኦፕሬሽን ዋና መቀመጫዋን ከአይፍል ታወር ጀርባ አድርጋለች።

“የዩናይትድ ኪንግደም ዋና መቀመጫ ከከተማው ማዕከል የራቀ ነበር። እኛ ወደ ማዕከሉ እንድንቀርብ መክረውናል። ኃላፊነቱ ወደተሰጣቸው ፖለቲከኞች እና ፖሊሶች እንድንቀርብም ምክራቸውን ለግሰዋል” ብለዋል ዋና አዛዡ።

250 የዩናይትድ ኪንግደም ኃይሎች እና 50 የፖሊስ ውሾች በፈረንሳይ ይገኛሉ።

ከስፔን፣ ከጀርመን፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከኳታር የተውጣጡ ወደ 1,750 ፖሊሶችም ተሰማርተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ ፖሊስ ማስተበበሪያ ማዕከል ዋና አዛዥ ማት ላውለር እንዳሉት፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የዩኬ ዜጎች ዝግጅቱን ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዩኬ በዚህ መጠን ሠራዊቷን በሌላ አገር ስታሰማራ ይህ የመጀመሪያው መሆኑንም አክለዋል።

ኦሊምፒክን በተመለከተ የተለየ የደረሰው ዛቻ እንደሌለ የፈረንሳይ ፖሊስ ገልጿል። ሆኖም ግን ከአገር ውስጥ እና ከውጭም ‘ወታደራዊ የሽብር ጥቃቶች’ ስጋት ሊኖር እንደሚችል አስታውቋል።

ትኬት መቁረጫ ወይም ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎች ላይ የበይነ መረብ ጥቃት እንዳይደርስም ጥበቃ እየተደረገ ነው።

ፈረንሳይ ለኦሊምፒክ እያደረገች ካለው ዝግጅት ጋር በተያያዘ ፍርሃት ለመፍጠር የበይነ መረብ ዘመቻ እንዳለ እና ከዚህም ጀርባ ሩሲያ አለችበት ተብሎ እንደሚታመን የፈረንሳይ መንግሥት አስታውቋል። በዚህም ቁጣውን ገልጿል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን “የመረጃ ጣልቃ ገብነት እና ማወክ እየተካሄደ ያለው በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ነው። በቅርበት እየተከታተልናቸው ነው። ሞኝ አይደለንም። ኦሊምፒክን የማክበር ሕግ በሁሉም አገራት ይተገበራል ብለን እናምናለን” ብለዋል።

እገታ ቢከሰት ምን ማድረግ እንደሚቻል ፖሊሶች በፓሪስ አቅራቢያ ልምምድ ሲያደርጉም ነበር።

እአአ በ2015 በባታክላን የሽብር ጥቃት ወቅት በቦታው የተሰማሩ ልዩ ፖሊሶች ናቸው ልምምዱን ያደረጉት።

የልዩ ፖሊሶቹ ኃላፊ ኮማንደር ሳይመን ሪዮንዴት “ከሁለት ዓመት በላይ ለኦሊምፒክ ስንዘጋጅ ነበር። እርምጃ እንድንወስድ የሚያስገድድ ነገር እንደማይከሰት ተስፋ አለን” ብለዋል።