ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንስሳት ከአንበሳ በላይ የሰውን ድምጽ እንደሚፈሩ በደቡብ አፍሪካ የተደረገ ጥናት አመለከተ
በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተደረገ ጥናት የዱር አጥቢ እንስሳት ከአንበሳ ይልቅ የሰዎች ድምጽ የበለጠ እንደሚያስፈራቸው አመለከተ።
ተመራማሪዎቹ ጥናቱን ለማከናወን በክሩገር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በሚገኝ ፏፏቴ የሰዎችን ንግግር የሚያሰማ የድምጽ ማጉያ ተጠቅመዋል።
የሰዎችን የንግግር ድምጽ ከሰሙት እንስሳት 95 በመቶ የሚሆኑት እጅግ በርግገው ‘እግሬ አውጪኝ’ ብለዋል።
በተቀራኒው እንስሳቱ በድምጽ ማጉያው ለተከፈተው የተቆጡ የአናብስት የማጉረምረም ድምጽ እጅግ ዝቅ ያለ ፍራቻን አሳይተዋል።
የተቀረጸው የሰዎች የንግግር ድምጽ ውስጥ በአገሪቱ በስፋት የሚነገር ቋንቋ ተካቶበት ነው እንስሳቱ እንደሰሙት የተደረገው።
ጥናቱ በተከናወነበት ጊዜ የአንበሳ ድምጽ በድምጽ ማጉያው የተሰማ ሲሆን፣ የተወሰኑ ዝሆኖች የድምጹን አቅጣጫ ተከትለው ለመጋፈጥ ሲሞክሩ ታይተዋል።
ጥናቱ አጋዘን፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ እና ነብርን ጨምሮ ልዩ ልዩ እንስሳት በሰዎች ስለሚታደኑ እንዲሁም መሳሪያና ውሻ በመጠቀም ስለሚያሳድዷቸው ከሰዎች ጋር መገናኘት እጅግ አደገኛ መሆኑን ተረድተዋል ይላል።
ጥናቱ ከደቡብ አፍሪካ ውጪም በዓለም ዙሪያ ያሉ የዱር እንስሳት ከየትኛውም አዳኝ በላይ የሰው ልጅን እንደሚፈሩ አዝማሚያዎቹ ያሳያል ሲልም ገልጿል።
ይህ ሁኔታ በዱር እንስሳት ቱሪዝም ላይ ለተመረኮዙ አካባቢዎች ፈተና እንደሚሆን አጥኚዎች አመልክተው፣ ምክንያቱን ሲጠቅሱም ሰዎች ሊያይዋቸው የሚፈልጓቸው እንስሳት እነሱኑ በመፍራት ስለሚሸሹ እንደሆነ ተገልጿል።
ከአጥኚዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ሊያና ዛናቴ ጥናቱ “የሥነ ምኅዳር ፍራቻ” ላይ ያተኩራል ብለዋል። “የሥነ ምኅዳር ፍራቻ” የአዳኝ እና ታዳኝ ግንኙነት በከባቢ ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ የሚገመግም ነው።
ተመራማሪዋ “አዳኞች ታዳኞችን ይገድላሉ። ያ ደግሞ ያለጥርጠር ቁጥራቸውን ይቀንሰዋል። ግን እኛ በጥናታችን ያሳየነው ደግሞ የታዳኞች አዳኞቻቸውን መፍራርት በራሱ ቁጥራቸውን ሊቀንሰው እንደሚችል ነው” ብለዋል።
ጨምረውም የሰው ልጆች በእንስሳት ላይ ከሚፈጥሩት ፍርሃት ጭምር ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ጥናቱ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ እንስሳት በሥነ ምኅዳር ውስጥ ሊደረግላቸው የሚገባውን ጥበቃም ጠቁሟል። የሰዎች ድምጽ በግባቡ ጥቅም ላይ ከዋል ሕገ ወጥ አደንን ለመከላከል ይረዳልም ይላል።