ፈረንሳያዊው ጋዜጠኛ ዩክሬን ውስጥ ተገደለ

ፌዴሪክ ሌሴሪክ ኢሞፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፌዴሪክ ሌሴሪክ ኢሞፍ

በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል ሲቬርዶንስቲክ በተሰኘችው ከተማ አቅራቢያ በሥራ ላይ የነበረ ፈረንሳያዊ ጋዜጠኛ መገደሉ ተሰምቷል።

ፌዴሪክ ሌሴሪክ ኢሞፍ የተባለው የ32 ዓመቱ ጋዜጠኛ ቢ ኤፍ ኤም ቲቪ ለተባለው የፈረንሳይ ጣቢያ በዩክሬን ከጦርነት የሚወጡበትን ዘመቻ በተመለከተ ዘገባ እየሰራ እየሰራ ሳለ ነው የተገደለው።

ጋዜጠኛው ሲጓዝበት የነበረው ጥበቃ ያለው ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ አንገቱ አካባቢ ጉዳት በመድረሱ ለህልፈት እንዳደረገው ባለስልጣናቱአሳውቀዋል።

ጋዜጠኛው የዩክሬንን ጦርነት ለመዘገብ ሲያቀና ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በተቀጠረበት ቢ ኤፍ ኤም ቲቪ ለ6 ዓመታት ሰርቷል።

ይሰራበት የነበረው ጣቢያ የጋዜጠኛውን ሞት አስመልክቶ በበይነ መረብ ባሰናዳው ዝግጀት “ይህ አሳዛኝ ክስተት ከሶስት ወራት በላይ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ግጭቱን እየዘገቡ ያሉ ሁለንም ጋዜጠኞች እንድናስታውስ አድርጎናል” ሲል አስፍሯል።

ጋዜጠኛው ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ እየተጋሩ ያሉ አሰቃቂ ምስሎች በደም የተበከለ እና የተጎዳ ተሽከርካሪን ንደሚያሳይ በስፈራው ያለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ አረጋግጧል።

ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ጋር ሲጓዝ የነበረ ዩክሬናዊ ጋዜጠኛ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከአደጋው ተርፏል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጋዜጠኛውን ሞት ተከተሎ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ በጦርነት ቀጠና ውስጥ እየሰሩ ያሉ ጋዜጠኞችን “የፈረንሳይ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደማይለያችሁ አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

“ጋዜጠኛ ፌዴሪክ ሌሴሪክ ኢሞፍ በዩክሬን ያለውን እውነታ ለማሳየት በቦታው ነበር። ከሩሲያ ቦምቦች ለመሸሽ ሲቪል ሰዎችን አሳፍሮ ከነበረ አውቶብስ ጋር ተተኩሶበት ሞቷል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን እንደተፈጠረ የሚያመላክት “ግልጽ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድ” ጠይቋል።

በዩክሬን ጦርነት በተቀሰቅሰበት ወር አሜሪካዊው ጋዜጠኛብሬንት ሪናው የተገደለ ሲሆን ጦርነቱን ሲዘግብ የተገደለ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ነው።