ፈረንሳይ በቻምፒየንስ ሊግ ለተፈጠረው ግርግር የሀሰተኛ ቲኬቶች ሽያጭን ተጠያቂ አደረገች

አስለቃሽ ጭስ የተተኮሰባቸው የሊቨርፑል ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አስለቃሽ ጭስ የተተኮሰባቸው የሊቨርፑል ደጋፊዎች

ባሳለፍነው ቅዳሜ ከተካሄደው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ቀደም ብሎ ለተፈጠረው ግርግር መነሻው ሀሰተኛ የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶች መሆናቸውን የፈረንሳይ ፖሊስ አስታውቋል።

የአገሪቱ ኃላፊዎች ጨዋታውን ለማየት ተሰብስቦ የነበረው ህዝብ ቁጥር ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደነበረ ባይሸሽጉም የተደራጀ ሃሰተኛ የቲኬት ሽያጭ ግን ለግርግሩ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የሊቨርፑል ደጋፊዎች ቲኬታቸውን ይዘው ሲጠባበቁ የነበረ ሲሆን የፈረንሳይ ፖሊስ ደግሞ ምንም ያላደረጉ ደጋፊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱ ተዘግቧል።

በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ስታድ ዴ ፍራንስ ስታዲየም የተደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ እስከ ምሽቱ አራት ተኩል ድረስ ያልተጀመረ ሲሆን በዚህ ጨዋታም ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን 1 ለ0 ረትቷል።

''ፖሊስ ደጋፊዎችን ያስተናገደበት መንገድ በጣም አሳፋሪ ነበር'' ብሏል ቶም የተሰኘ የሊቨርፑል ደጋፊ። ''ቲኬት ይዘው ይጠባበቁ የነበሩ ደጋፊዎችም ጭምር ላይ ነበር ፖሊስ አስለቃሽ ጭሱን ሲለቅ የነበረው።

ደጋፊዎቹ ጨዋታውን ለመመልከት እስከ ሁለት ሰአት ድረስ ነው ሲጠብቁ የነበረው። ነገር ግን ድንገት ፖሊስ መጥቶ በአስለቃሽ ጭስ ሊበትናቸው ሲሞክር ነበር''

ማይክል ካርተር የተባለ አንድ ሌላ ደጋፊ ደግሞ ለቢቢሲ ሲናገር ''ከኋላ የነበሩ ደጋፊዎች በጭሱ ታፍነው የነበሩ ሰዎችን ሲረዱና ሲደግፉ ነበር'' ብሏል።

ክስተቱን ተከትሎ በተለይ የዩኬ ዜጎችና ኃላፊዎች ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን የፈረንሳይ ስፖርት ሚኒስቴርም ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እንዲሁም፣ ከፈረንሳይ እግር ኳስ ማህበር፣ ከስታዲየም ኃላፊዎች እንዲሁም ከፖሊስ ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በበኩሉ ከፍጻሜው ጨዋታ ጋር በተያያዘ ገለልተኛ ምርምራ እያደረገ ሲሆን የፈረንሳይ መንግስት የሚያደርገው ምርመራ በአስር ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል። የፈረንሳይ የአገር ውስጥና የስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለተፈጠረው ግርግር ምክንያቶቹ በዋነኛነት ነውጠኛ ደጋፊዎችና ሐሰተኛ ቲኬቶች መሆናቸውን አስረግጠዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ጌራልድ ዳርሚየን እንዳሉት በሪያል ማድሪድና ሊቨርፑል መካከል በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ወቅት በተደራጀ መልኩ ተዘጋጅቶ ይሸጥ ነበር። አክለውም ከዚሁ ጋር በተያያዘ 30 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የእንግሊዝ ዜጎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

''ከ30ሺ እስከ 40 ሺ የሚደርሱ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ሐሰተኛ ቲኬቶችን ይዘው አልያም ምንም ቲኬት ሳይኖራቸው ነው ወደ ስታዲየም ለመግባት ሲሞክሩ የነበረው። ፖሊስ የወሰደው እርምጃ ከትልቅ ቀውስና ሰው ሕይወት መጥፋትን ነው የተከላከለው'' ብለዋል።

የፈረንሳይ ስፖርት ሚኒስትሯ ኤምሊ ካስቴራ ከአንድ የሬድዮ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ከስፔን የመጡት የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ምንም አይነት ችግር አልፈጠሩም ነበር። የስፔን ኃላፊዎች ደጋፊዎቻቸውን ከሊቨርፑል በተሻለ መልኩ ተቆጣጥረዋቸዋል'' ሲሉ ተደምጠዋል።