በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የቡርኪናፋሶ መሪዎች የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተደረገባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቡርኪናፋሶ የደኅንነት እና የፀጥታ ኃይሎች ማክሰኞ የተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማክሸፋቸውን በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት አስታወቀ።
የመንግሥት ግልበጣ ሙከራውን ያደረጉት ወታደራዊ መኮንኖች እና ሌሎች ቡርኪናፋሶ ውስጥ አለመረጋጋትን በመፍጠር ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አቅደው ነበር ሲል ወታደራዊው አስተዳደር ከሷል።
በአሁኑ ወቅት የቡርኪናፋሶ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከጨበጡ አንድ ዓመት እንኳን አልሞላቸውም።
ከእስላማዊ አማጺያን ጋር ውጊያ ውስጥ የምትገኘው ቡርኪናፋሶ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ውስጥ ብቻ ሁለት ጊዜ የመንግሥት ግልበጣ ተካሂዶባታል።
ስለመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ በአገሪቱ ቴሌቪዥን በቀረበው መግለጫ ላይ፣ ምንም አይነት ዝርዝር ማብራሪያ ሳይሰጥ የተወሰኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
በአገሪቱ ጦር ኃይል ውስጥ ቅሬታዎች እንዳሉ በቅርቡ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።
ባለፈው ማክሰኞ በሠራዊቱ ውስጥ አመጽ መቀስቀሱን የሚገልጹ ወሬዎች መሰማታቸውን ተከትሎ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የወታደራዊው መንግሥት ደጋፊዎች አመጹን በመቃወም በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ አድርገው ነበር።
የዚያኑ ዕለትም በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚታተመው “ዤን አፍሪክ” የተባለው የዜና መጽሔት የአገሪቱን ጦር ኃይሎች ስም የሚያጠፋ ጽሁፍ አትሟል በሚል በባለሥልጣናት እገዳ ተጥሎበታል።















