ወደ ሰሜን ኮሪያ ያለ ፈቃድ የገባው አሜሪካዊ ወታደር በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ነው ተባለ

ትራቪስ ኪንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሰሜን ኮሪያን ድንበር ተሻግሮ ያለ ፈቃድ የገባው አሜሪካዊ ወታደር ትራቪስ ኪንግ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ባለስልጣናት ተናገሩ።

በሁለቱ አገራት መካከል መወዛገቢያ የነበረው ትራቪስ ከሰሜን ኮሪያ መባረሩ ተገልጿል።

ትራቪስ በአሜሪካ በሚገኝ ወታደራዊ ተቋም ከመወሰዱ በፊት ለአሜሪካ ተላልፎ የተሰጠው በቻይና ነው።

የ23 ዓመቱ ወታደራዊ የስለላ ባለሙያ ከጥቂት ወራት በፊት ነበር የሰሜን ኮሪያ ድንበርን በሕገወጥ መንገድ ተሻግሮ ወደ አገሪቱ የገባው።

ጥቁሩ ወታደር በአሜሪካ ጦር ሰራዊት ውስጥ ባለው “ኢሰብዓዊነት እና ዘረኝነት” ምክንያት ተሰዷል ሲሉም የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ እና አሜሪካ ካደረጉት የበርካታ ወራት የዲፕሎማሲ ውዝግብም በኋላ ትራቪስ በአሜሪካ ጥበቃ ሥር መሆኑን እና ቤተሰቡንም እንዳናገረ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።

“ትራቪስ ኪንግ ወደ ቤቱ እየሄደ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን እርግጠኞች ነን። ከቤተሰቡ ጋር ለመገናኘትም በከፍተኛ ጉጉት ላይ ነው” ሲሉም ነው ባለስልጣኑ የተናገሩት።

“ከቤተሰቦቹ ጋር ሲገናኝ በጥሩ መልኩ እንዲሆንና ማንኛውንም የህክምና እና ሌሎች ስጋቶችንም ለመፍታት ዳግም ውህደት የሚያደርግበትን ሂደት እንመራዋለን” በማለት ባለስልጣኑ አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ አክለውም ሰሜን ኮሪያ ወታደሩን እንድትለቀው አሜሪካ ምንም አይነት ስምምነት አልፈጸመችም ብለዋል።

ትራቪስ በቻይናዋ የድንበር ከተማ ዳንዶንግ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ከተገናኘ በኋላ በውጭ ጉዳይ ቢሮ አውሮፕላን ደቡብ ኮሪያ ወደሚገኘው የአሜሪካ አየር ማረፊያ ተወስዷል።

የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃለ አቀባይ ማቲው ሚለር እንደተናገሩት ወታደሩ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የአሜሪካን መሬት ይረግጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት የዜና ወኪል በበኩሉ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሳይሰጥ ትራቪስ ኪንግ እንዲባረር መወሰኑን ባለፈው ረቡዕ ዘግቦ ነበር።

አሜሪካዊው ወታደር ትራቪስ ኪንግ የሰሜን ኮሪያን ድንበር ዘልቆ ከመግባቱ በፊት በደቡብ ኮሪያ በጥቃት ክስ ለሁለት ወራት በእስር ቤት አሳልፏል። የተለቀውም ከወር ገደማ በፊት ነው።

ወታደሩ ከነበረበት ደቡብ ኮሪያ በሥነ ምግባር ምክንያት ወደ አሜሪካ ሊመለስ በዝግጅት ላይ እያለ ነው ይህ ሁኔታ የገጠመው።

ትራቪስ ወደ አሜሪካ ሊመለስ የበረራው ጊዜ በቀረበበት ወቅት ባልታወቀ ሁኔታ ቀድሞ ወዳዘጋጀው የድንበር አካባቢ ለጉብኝት ተጓዘ።

ይህን ያደረገበት ምክንያት ባይታወቅም የአሜሪካ የጦር ባለስልጣናት ግን ወታደሩ በፈቃዱ ድንበሩን እንደተሻገረ ተናግረዋል።

ከወራት በፊት ሰሜን ኮሪያ አሜሪካዊው ወታደር ድንበሯን አቅርጦ የገባው በጦሩ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ አያያዝ እና ዘረኝነት ለመሸሽ እንደሆነ ከገለጸች በኋላ ምላሽ የሰጡ አንድ የፔንታገን ባለሥልጣን ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ወታደር ኪንግን “በተገኘው መንገድ” በሰላም ወደ አገሩ መመለስ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።