በሐሰት ታግቻለሁ ያለው አውስትራሊያዊ ለፖሊስ ካሳ እንዲከፍል ታዘዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያዊው ግለሰብ በሐሰት ታግቻለሁ ካለ በኋላ ለፖሊስ ካሳ እንዲከፍል ታዘዘ።
በኒው ሳውዝ ዌልስ፣ ወሎንጎንግ ነዋሪ የሆነው ፖል ሌራ ይህን ሴራ ያዘጋጀው የአዲስ ዓመት ዋዜማን በትዳር አጋሩ ፋንታ ከሌላ ሴት ጋር ለማሳለፍ ነበር።
የ35 ዓመቱ ግለሰብ የፈፀመው ድርጊት ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤትም ፖሊስ ምርመራ ላካሄደበት10 ሺህ 334 ዶላር ለኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ እንዲከፍል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የወሎንጎንግ ዳኛ “ሌራ ያቀረበው ሐሳብ በትንሹም ቢሆን አሳማኝ ምክንያት ነበር “ ብለዋል።
ሌራ ከአጋቾቹ እንደሆነ በመግለጽ ለትዳር አጋሩ የጽሑፍ መልዕክት የላከው እንደ አውሮፓውያኑ ታኅሳስ 31 2022 ላይ ነበር። ጽሑፉ የፈጠራቸው አጋቾቹ እስከ ጠዋት ድረስ እንደሚያቆዩት ይገልጻል።
ከዚያም አጋሩ በሌክ ኢላዋራ ዲስትሪክት ፖሊስ ሪፖርት አድርጋለች። ፖሊስ ባደረገው ክትትልም በሚቀጥለው ቀን ሌራን በትውልድ ከተማው ዳፕቶ ሊያገኘው ችሏል።
ሌራ ታግቻለሁ ሲል ያቀረበውን ክስ ለመመርመር የፖሊስ መኮንኖች ለፍለጋ ከ200 ሰዓት በላይ ያሳለፉ ሲሆን የስልክ ልውውጦችን ለመፈለግ እና ለክፍያ 16 ሺህ 218 ዶላር ገንዘብ እንዳወጡ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአገሪቷ ጋዜጣ ኢላዋራ ስታር እንደዘገበው ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ በማይታወቁ የመካከለኛው ምስራቅ ወንዶች የተወሰደ መሆኑንና በኋላ ላይ እንደለቀቁት ተናግሯል።
ግለሰቡ በሐሰት ወንጀላ ሌሎች ሰዎች እንዲመረመሩ አድርጓል በሚል በሰባት ዓመት እስር ሊያስቀጣ የሚችል ክስ ቀርቦበት ጥር ወር ላይ ታስሮ ነበር።
ሌራ እስራቱ የቀረለት ሲሆን የሦስት ዓመት የማኅበረሰብ እርማት እና የ350 ሰዓት የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም ለፖሊስ ካሳ እንዲከፍል ታዟል።
በተጨማሪም ከዚህ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው፣ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ ፣ የተከለከለ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶች ያለፈቃድ በመያዝ ሦስት ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
ዳኛ ማይክል ኦንግ የሌራን ድርጊት “አጸያፊ “ እንዳሉት የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የሌራ ጠበቃ አባስ ሶኬ በበኩላቸው የደንበኛቸው የእስር ጊዜ በመቅረቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሕግ ጥሰቱ በኋላ ደንበኛቸው ብዙ እርምት እንደወሰደ እና የቤተሰቦቹንና የአጋሩን ድጋፍ ማግኘት እንደቀጠለ እንዲሁም ስኬታማ የማኅበረሰብ አባል በመሆን ሕይወቱን መቀጠል እንደሚፈልግ ጠበቃውን ጠቅሶ 9ኒውስ ዘግቧል።












