አዲስ አበባ እና ክልሎች ከአማራ ሕዝብ እና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን አሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የክልል መስተዳደሮች ከአማራ ሕዝብ እና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ በአማራ ክልል ያጋጠመውን ቀውስ እና ታጣቂ ኃይል እንታገላለን አሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ እና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች ባወጡት መግለጫ፣ በአማራ ክልል በሕገ-ወጥ ቡድን ተፈጥሯል ያሉትን አመጽ በጽኑ አውግዘው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
ክልሎቹ ተመሳሳይ ይዘት ባለው መግለጫቸው በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቷል፣ መከላከያ እየተተነኮሰ ነው እንዲሁም የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ኅልውና የሚያስጠብቅ አገራዊ ተቋም ነው ብለዋል።
ክልሎቹ ይህን ያሉት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ተባብሶ የፌደራሉ መንግሥት ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስት ከፍሎ የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ እቆጣጠራለሁ ባለበት ወቅት ነው።
ለወራት የቆየው እና ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት የተጠየቀበት የፀጥታ መደፍረስ፤ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለ ግጭት መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ግጭት ሳቢያ በክልሉ አብዛኛው ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ፍጥጫ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።
ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ባወጡት በመግለጫ፣ እራሳቸውን በፋኖ ስም አደራጅተው በአማራ ክልል አመጽ ያስነሱትን ታጣቂ ኃይሎች “ሕገ-ወጥ፣ ጽንፈኛ፣ ጃውሳ፣ ዘራፊ ቡድን እና አፍራሽ ኃይል” በማለት የገለጿቸው ሲሆን፣ ዓላማቸውም በሕዝብ ጥያቄ ሽፋን በአቋራጭ ሥልጣን ለመቆጣጠር ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ክልሉን ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እየከተተ ነው ያሉት ክልሎቹ እና የከተማ አስተዳደሩ፤ ከአማራ ሕዝብ እና መንግሥት ጎን በመሰለፍ ይህንን ኃይል በጽናት እንታገላለን ብለዋል።
ክልሎቹ መጨረሻም መንግሥት እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉ ወደ ቀደመው ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንደሚመለስ ሙሉ እምነት አለን ብለዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ባውጣው መግለጫ የዚህ የጥፋት ቡድን ለእኩይ ዓላማው ማስፈፀሚያነት የሚያገለግሉ እና ምንም አይነት ግጭት ከሌለበት አካባቢ ከግጭት የሸሹ ተፈናቃይ በማስመሰል "በርካታ ፀጉረ-ልውጦችን አስርገው ወደ መዲናዋ በማስገባት የአመፅ አላማቸውን ለማራመድ ሲሞክሩ ተይዘዋል" ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስምንት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ በአማራ ክልል ችግር በከፍተኛ ጥንቃቄ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጥሪ አቀረቡ።
በሕግ እና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሠሩት ሲቪክ ማኅበራት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱባቸውን መፍትሄ እንዲያገኙ ሁሉም ወገኖች ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ሰብዓዊ መብቶች እና ሰብዓዊ ሕግጋትን ያከበሩ እንዲሆኑ እና የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ፤ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ጾታዊ ጥቃቶች እና ሌሎችም እንዳይደገሙ ጥረት እንዲደረግ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል።












