ብዙዎች ‘እንቅልፍ እንዲጥላቸው’ ያደረገውን ድምጽ አልባ ‘አላርም’ እንደሚያስተካክል አፕል ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንዳንድ አይፎን ስልኮች ከእንቅልፍ መቀስቀሻ ጥሪ (አላርም) ድምጽ አልባ መሆኑ ተጠቃሚዎችን እያማረረ ነው።
እንቅልፍ ጥሏቸው እያረፈዱ መሆኑንም ተናግረዋል። አፕል ችግሩን በአፋጣኝ ለመቅረፍ እየሠራሁ ነው ብሏል።
አንድ የአይፎን ተጠቃሚ “አምስት ጊዜ አላርም ብሞላም ምንም ድምጽ አላሰማም” ስትል ቲክቶክ ላይ ቅሬታዋን አሰምታለች።
አፕል ችግሩ መከሰቱን ቢያውቅም ለምን እንደተከሰተና ተጠቃሚዎች እንዴት ችግሩን መቅረፍ እንደሚችሉ ገና አልደረሰበትም።
ምን ያህል ተጠቃሚዎች በዚህ ችግር ውስጥ እንደወደቁም ግልጽ አይደለም።
ዜናው መጀመሪያ የተሰማው ከኤንቢሲ የማለዳ ዝግጅት ‘ቱደይ ሾው’ ነው።
ችግሩ መፍትሄ እስከሚያገኝ ተጠቃሚዎች አላርማቸውን ድምጹን ከፍ አድርገው መተኛት እንዳለባቸው ተገልጿል።
አፕል ተጠቃሚዎቹ ስልካቸው ላይ ምን ያህል እንዳተኮሩ የሚፈትሽበት አሠራር መዘርጋቱ ለችግሩ መነሻ ነው ብለው የወቀሱም አልታጡም።
ይህ ማለት ተጠቃሚዎች ስልካቸው ላይ ትኩረታቸው እንዳልሆነ ስልኩ ሲገነዘብ ድምጽ ይቀንሳል ማለት ነው።
ይህ አሠራር በአይፎን ኤክስ እና አይፓድ ፕሮ 11 ኢንች እንዲሁም አይፓድ ፕሮ 12.9 ኢንች ላይ ይገኛል።












