ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ራስ ምታት የሆነው በሦስት እጥፍ የናረው የማዳበሪያ ዋጋ

“ዘንድሮ በሦስት እጥፍ በጨመረው የማዳበሪያ ዋጋ ምክንያት በመጪው ዓመት ልንራብ እንችላለን የሚል ስጋት አድሮብናል” ይላሉ አርሶ አደር አቡ ማሞ።

ባለፈው ዓመት በዝናብ እጥረት ምክንያት ምርት እንደተበላሸባቸው የሚናገሩት አቶ አቡ፣ ዘንድሮው በጊዜ ወደ ግብርና እገባለሁ ብለው ቢያስቡም፣ ላለፉት ስምንት ወራት ሰማዩ በመራቆቱ ስጋት ውስጥ ወደቀዋል።

በዚህ ዓመት ባጋጠማቸው ድርቅ ምክንያት የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ከብቶቻቸው ማለቃቸውን የሚናገሩት የአርሲ ዞን አርሶ አደሩ፣ “ሸጠን ማዳበሪያ የምንገዛበት እንኳ የለንም” ሲሉ የችግራቸውን ተደራራቢነት ይገልጻሉ።

“ከዚህ በፊት መቶ ኪሎ ማዳበሪያ በ1600 ብር ነበር የምንገዛው። ዘንድሮ ግን 5000 ብር ደርሷል። ገበሬ ቀለቡን እንኳ ማሟላት አቅቶታል። በዚህ ምክንያት ማደበርያ መግዛት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል።”

መጀመሪያ ላይ የአፈር ማዳበሪያ ራሱ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር በማንሳት፣ አሁን ግን መንግሥት እያቀረበላቸው መሆኑን ይናገራሉ።

መንግሥት ቢያቀርብላቸውም ዋጋው በጣም በመጨመሩ የተነሳ እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ለመግዛት ከብዷቸዋል።

አርሶ አደር አቡ በደላሎች የሚሸጠው ማዳበርያም ቢሆን መንግሥት ከሚያቀርብበት የበለጠ ውድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አቶ ገበየሁ ሙኩይ በበኩላቸው፣ ባለፈው ዓመት የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ 1800 እንደነበር ያስታውሳሉ።

በዚህ ዓመት ግን 4000 የኢትዮጵያ ብር መድረሱ ኪሳቸውን ፈትኖታል።

“እስካሁን ድረስ አቅም ያለው አርሶ አደር ካልሆነ በስተቀር ሰዎች ማዳበሪያ መግዛት አልቻሉም። ያለፈው ዓመትም አዝመራ በዝናብ ምክንያት ጠፍቷል። በዚህም ምክንያት ከብቶቻችንን ሽጠን እንኳ የምንገዛበት አቅም የለንም” ብለዋል አቶ ገበየሁ።

በአፈር ማዳበርያ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ምርታቸው በዝናብ ምክንያት ከመጥፋቱ ጋር ተያይዞ ለእለት ምግብ ጭመር መቸገራቸውን ይናገራሉ።

አቶ ገበያሁ “በፊት አርሶ አደሩ ከብቶችን አደልቦ በመሸጥ ማዳበርያ ይገዛበት ነበር። ዘንድሮ ግን ይህም ከባድ ሆኖብናል” ብለዋል።

አክለውም አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ፊት ረሃብ ይገጥመን ይሆን የሚል ስጋት ውስጥ ገብተናል ሲሉ ስጋታቸውን ያጋራሉ።

ሌላኛው ከሆሮ ጉዱሩ ዞን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደርም፣ በዚህ ዓመት የማዳበሪያ ዋጋ እንደ ከበዳቸው ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት በ1ሺህ 600 ብር ይገዙት የነበረው ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዚህ ዓመት 5ሺህ 300 ብር መድረሱን ገልፀዋል።

በአካባቢያቸው ባለው የሰላም ችግር ምክንያት ስሜ አይጠቀስ ያሉት እኚህ አርሶ አደር፣ የዘንድሮ የማዳበሪያ ዋጋ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖብናል በማለት በአካባቢያቸው ያለው የሰላም እጦት ላይ ይህ የዋጋ ንረት መከሰቱ ኑሯቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደጣለው ገልፀዋል።

ማሳቸው ካለማዳበሪያ ምርት መስጠት እንደማይችል የሚናገሩት እኚሁ አርሶ አደር፣ የአየር ሁኔታ መለወጡ በራሱ ሌላ ችግር መሆኑን ያነሳሉ።

መንግሥት ምን ይላል?

የግብርና ሚኒስቴር ኢትዮጵያ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሟን ያስታወቀው በሚያዚያ ወር ነበር።

በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶ/ር ሶፊያ፣ የማዳበሪያ ዋጋ ስለመናሩ ተጠይቀው ሲመልሱ “የግዥ ስምምነቱ ቀድሞ ስለተፈፀመ እንጂ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ጭማሪው ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችል ነበር” ብለዋል በወቅቱ።

በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ 5.6 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ማዳበሪያ ተገዝቶ ለገበሬዎች እየተሰራጨ መሆኑን በክልሉ የግብርና ቢሮ የምርት ግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ታከለ ቁሩንዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለክልሉ በዘንድሮው ዓመት ተገዝቶ ወደ አገር እንዲገባ የታቀደው 8 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን የተናገሩት አቶ ታከለ፣ እስካሁን እንዲገዛ የተፈቀደው 5.5 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ውስጥ አልገባም ያሉት ኃላፊው፣ ባለፈው ዓመት ተገዝቶ፣ መጋዘን ውስጥ የተቀመጠ 800 ሺህ ኩንታል ተጨምሮበት፣ 5.6 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለገበሬው መሰራጨቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስካሁንም ወደ 3.2 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ማዳበርያ አርሶ አደሮች እጅ መድረሱን አረጋግጠዋል።

የማዳበሪያ ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን የሚናገሩት እኚሁ ኃላፊ፣ ዋጋውም በዘንድሮው ዓመት በ3 እጅ (300%) እጅ መጨመሩን ተናግረዋል።

ለዚህም ምክንያቱ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እና ዓለም ከገባችበት ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያነሳሉ።

አሁን የተገዛው ማዳበሪያ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳድሮ የገዙት መሆኑን በማንሳት ከዚህ በፊት ማዳበሪያን ሲያመርቱ የነበሩት አገራት በተለያዩ ምክንያቶች ዘንድሮ እንደ በፊቱ ማምረት አለመቻላቸውን አንስተዋል።

አሁን ባለው ዋጋ መግዛት የማይችሉት አርሶ አደሮችም በብድር መልክ የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ታከለ ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ገበሬዎች በአካባቢያቸው በሚያገኙት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይንም ኮምፖስት በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ አንደ አማራጭ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

ይኹን እንጂ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ሄክታርን ለማዳረስ መቶ እና ከዚያ በላይ ኩንታል የሚያስፈልግ ስለሆነ ይህን ያህል ማዘጋጀት ለገበሬው ከባድ ሊሆን እንደሚችልም አንስተዋል።

ለአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር ምክንያቶች

ሚኒስትር ዲኤታዋ ለዋጋ ጭማሪው እንደ ዋና ምክንያትነት የሚያነሱት በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዳበሪያ ዋጋ መናርን ነው።

ትላልቅ የማዳበሪያ አምራች አገራት በኮቪድ-19 ምክንያት ምርታቸውን በመቀነሳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት መከሰቱን ሚኒስቴር ዲኤታዋ ያስረዳሉ።

በተለይ ደግሞ ዩሪያ ለተባለው ማዳበሪያ ማምረቻ የሚያገለግል የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በመጨመሩ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያመርቱት አገራት ከምርት ውጪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ቻይና እና ሩሲያ ወደ ውጪ የሚልኩትን ማዳበሪያ ውስን አድርገውት ስለነበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሆነ እጥረት መከሰቱን ሚኒስቴር ዲኤታዋ ለዋጋው መናር አስተዋጽኦ ያደረጉ ነገሮችን በምክንያትነት ይዘረዝራሉ።

 ዓለም ምግብ ድርጅት የማዳበርያ እጥረት ተጨማሪ ሌሎች 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ እጥረት ያጋልጣል ሲል አሳስቧል።

በ2022 (እኤአ) 45 ሚሊዮን የነበረው የብርዕ እህል ምርት ወደ 38 ሚሊዮን ቶን ዝቅ ይላልም ሲል አስጠንቅቋል።