ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማዳበሪያ ዋጋ መናር “መሬታችን ጦም ሊያድር ይችላል” ሲሉ አርሶ አደሮች ስጋታቸውን ገለጹ
በማዳበሪያ ዋጋ መናር ምክንያት " መሬታችን ምንም አዝዕርት ሳይዘራበት ሊከርም ይችላል" ሲሉ አርሶ አደሮች ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።
የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ከ150 በመቶ በላይ ጨምሯል። ይህም ለአርሶ አደሩ ራስ ምታት ከሆነ ሰነባብቷል።
በባለፈው ዓመት በኩንታል 1700 ብር ይሸጥ የነበረው ማዳበሪያ ዘንድሮ ዋጋው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 4200 ብር ገብቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች የዋጋ ንረቱ በምርታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ።
"የእኔ እቅድ በዚህ ዓመት ለማዳበሪያ እስከ 25 ሺህ ብር ድረስ አወጣለሁ የሚል ነበር። አሁን ግን ከእጥፍ በላይ ሆኖ ከ50 ሺህ ብር በልጧል። ታዲያ እንዴት አድርጌ እዘራለሁ?!" ሲሉ ይጠይቃሉ አርሶ አደር ጌቴ።
የዋጋ ንረቱ ማዳበሪያ የማይፈልጉ እና ዋጋ የማያወጡ ሰብሎችን መዝራትን እንደ አንድ አማራጭ እንዲያስቡም አስገድዷቸዋል።
አርሶ አደር ጌቴ "እስካሁን አንድም ማዳበሪያ አልገዛሁም፤ ለበጋ መስኖ ቀደም ብሎ ከሰው ተበድሬ የዘራሁትንም እንዴት እንደምከፍል ጭንቅ ሆኖብኛል" ይላሉ።
የሌላኛው አርሶ አደር ሹመት ጭንቀትም ተመሳሳይ ነው።
"የመንደራችን የማለዳና የምሽት ወግም የማዳበሪያ ጉዳይ ከሆነ ሰንብቷል" ይላሉ።
መሬታቸውን በአዝዕርት ለመሸፈን ቢያንስ 8 ኩንታል ኤንፒኤስ እና 4 ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው የገለፁት አርሶ አደሩ፣ ይህንን ለመግዛት አቅማቸው ስለማይፈቅድ የተሻለ መፍትሔ ካልተሰጠ ጭራሽኑ ማምረት እንደማይችሉ ይናገራሉ።
"እኔ ደሃ አርሶ አደር ነኝ። በተባለው ዋጋ ገዝቼ ማምረት አልችልም። እንደው ልጄቼ የሚቆርጡት እሸት እንዳያጡ ጥቂት በቆሎ እዘራ እንደሁ እንጂ ሌላማ ምኑን አመረትኩት" ይላሉ።
ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት 12.8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሟን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስካሁን ወደ አገር ውስጥ መግባት የቻለውንም ለክልሎች የማሰራጨት ሥራ መጀመሩን በሚኒስቴሩ የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶ/ር ሶፊያ ካሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ዋጋው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ150 በመቶ በላይ መጨመሩን የገለጹት ዶ/ር ሶፊያ፣ የግዥ ስምምነቱ ቀድሞ ስለተፈፀመ እንጂ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ጭማሪው ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችል ነበር ብለዋል።
ለመሆኑ የማዳበሪያ ዋጋ ለምን ጨመረ?
ሚኒስትር ዲኤታዋ ለዋጋ ጭማሪው እንደ ዋና ምክንያትነት የሚያነሱት በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዳበሪያ ዋጋ መናርን ነው።
" እንደ አገር ቀድመን ጨረታ አውጥተን ውል ስለገባን ነው አሁንም የተሻለ የሚባል ዋጋ ያገኘነው" ይላሉ።
ትላልቅ የማዳበሪያ አምራች አገራት በኮቪድ-19 ምክንያት ምርታቸውን በመቀነሳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት መከሰቱን ሚኒስቴር ዲኤታዋ ያስረዳሉ።
በተለይ ደግሞ ዩሪያ ለተባለው ማዳበሪያ ማምረቻ የሚያገለግል የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በመጨመሩ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያመርቱት አገራት ከምርት ውጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ቻይና እና ሩሲያ ወደ ውጭ የሚልኩትን ማዳበሪያ ውስን አድርገውት ስለነበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሆነ እጥረት መከሰቱን ሚኒስቴር ዲኤታዋ ለዋጋው መናር አስተዋጽኦ ያደረጉ ነገሮችን በምክንያትነት ይዘረዝራሉ።
በግዥ አፈጻጸሙ መዘግየት የተስተዋለውም በዚሁ ምክንያት ተደጋጋሚ ጨረታ ለማውጣት በመገደዳቸው እንደሆነ ያክላሉ።
ይሁን እንጂ አሁን እየገባ ያለውን ማዳበሪያ ቀድመው የሚዘሩ አካባቢዎችን በመለየት ክልሎች በአግባቡ እንዲያደርሱ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አርሶ አደሮች የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየተጠቀሙ ማምረት እንዲችሉ ክልሎች በከፍተኛ ንቅናቄ እየሰሩም ነው ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ግን የተፈጥሮን ማዳበሪያ እምብዛም እንደማይጠቀሙ እና መሬታቸው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንደተለማመደ በመግለጽ ያለውን ችግር ያስረዳሉ።
በመሆኑም መንግሥት የሚራዘሙ ፕሮጀክቶችን እያራዘመ አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳበሪያ እንዲያገኝ ድጎማ እንዲያደርግ የተሻለ ነው ያሉትን የመፍትሔ ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ይህንኑ የአርሶ አደሮቹን ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሚኒስትር ዲኤታዋ "በቀጣይ ታይቶ መንግሥት የሚወስደውን አቅጣጫ እናሳውቃለን። አሁን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው አቅርቦት ላይ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለውም ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከፈፀመችው 17 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የዘንድሮው ከ5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰው "አጠቃላይ ከነበረው ፍላጎት 70 በመቶ ግዥ ነው የተፈፀመው ፤ በበልግ ወቅት ተጨማሪ ግዥ ሊኖር ይችላል " ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዋናነት የማዳበሪያ ግዥ የምትፈጽመው ከአፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ መሆኑንም ዶ/ር ሶፊያ ገልጸዋል።