የአዲስ ዓመት ተስፋዬ 'ይህ በቃን' ብለን ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እንዲሆን ነው

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በመስከረም ወር 2005 ዓ. ም. ነበር የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ ኢትዮጵያን እንዲመሩ የተሾሙት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነትን ጨምሮ በበርካታ የክልል ብሎም የፌደራል የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በቦርድ አመራርነት ያገለግላሉ።

እንዲሁም ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ጋር ባቋቋሙት ፋውንዴሽን አማካኝነት በተለያዩ ተግባራትን ላይ እየተሳተፉ ነው።

አቶ ኃይለማሪያም በአፍሪካ ምርጫዎችን የመታዘብ ሂደቶችን መርተዋል። ቢቢሲ ከአቶ ኃይለማሪያም ጋር የ2015 አዲስ ዓመት አስመልክቶ አጭር ቆይታ አደርጓል።

መስመር

ቢቢሲ፡ ጡረታ ወጥተዋል ወይስ አሁንም መደበኛ ሥራዎች አለዎት? ኑሮዎትስ የት ነው?

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምኖረው። ነገር ግን የሥራዬ ሁኔታ ወደ ተለያዩ አገራት በተደጋጋሚ ያመላልሰኛል። በሁለት መስኮች በዋናነት እሳተፋለሁ።

የመጀመሪያው ሥራዬ በኃይለማሪያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ከባለቤቴ ጋር በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ እንሰራለን።

ቅድሚያ የሚሰጣቸው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ብሎም የተፈጥሮ ሃብት እና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ላይ እንሰራለን። ይህም የደን፣ የአፈር እና የውሃ፣ የእጽዋት እንዲሁም የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራዎች ላይ እናተኩራለን።

አገራችን በዚህ ጉዳይ በጣም የተጎዳች ናት። ከፍተኛ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች አሉባት። ድርቅ እና ጎርፍ ተመላልሰው ያጠቋታል።

ሥራችንን በኦሞ ስምጥ ሸለቆ ላይ እንጀምር ብለን እዚያ ጀምረናል።

የአካባቢው ኅብረተሰብ በአብዛኛው አርብቶ አደር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሕጻናት፣ የልጆች፣ የሴቶች ብሎም የወጣቶች ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ ነው።

ስለዚህም የጤና፣ የትምህርት እና የሥርዓተ ምግብ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ በዚሁ በኦሞ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ እየሰራን እንገኛለን።

ሌላኛው ግን የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የማደርገው ተሳትፎ ነው። ይህ ከልጅነቴ ጀምሮ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ስለሆነ ነው የትምህርት መስኬን ስመርጥ ወደዛው ያዘነበልኩት።

ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ መፍትሔዎች ላይ የቅስቀሳ ሥራዎች (Advocacy) ላይ በሰፊው እሳተፋለሁ። እንዲሁም በሰላም እና ፀጥታ አጀንዳ ላይ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ ውይይቶች ላይም ወረቀቶችን አቀርባለሁ እንዲሁም እሳተፋለሁ።

በአንድ ወቅት የዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ የቦርድ አባል ሆኜ እሰራ ነበር። አሁን በሥራ መደራረብ ምክንያት ትቼዋለሁ።

እንዲሁም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ፣ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ፣ ዴሞክራሲ እና የአመራር ሥራን የማቀላጠፍ ሥራዎች ላይ እሳተፋለሁ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ፡ አውደ ዓመትን እንዴት ያሳልፋሉ?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ ብዙ ጊዜ ከአውደ ዓመት በፊት በቤተክርስትያን ጾሞች አሉ። አዲሱም ዓመት ከመግባቱ 15 ቀናት ቀደም ብለን የጾም ጸሎት እናካሂዳለን። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት፣ የብልጽግና እንዲሆን ብሎም የተረጋጋ ሆኖ እንዲያልፍ እንጸልያለን።

ነገር ግን በየትኛውም በዓል ወቅት ግርግር ሲኖር ብዙም ደስተኛ አይደለሁም።

በእርግጥ በባሕሪዬ ብዙ ግርግር አልወድም። ይልቁንም ወደ ጫካ፣ ወንዝ ወይም ፓርኮች የመሄድ ልምድ አለኝ።

ቤት ውስጥ የምናሳልፍ ከሆነ ግን ቁጭ ብለን የምንጫወትበት ነው። ከሁሉም በላይ ዋናው የቤተሰብ ነውና፤ ቤተሰብ አንድ ላይ ይሰበሰባል።

በተለይም ማምሻ አካባቢ ሁሉም ሰው ከቸርችም ሆነ ከየቤታቸው ይሰበሰባሉ፤ እንጫወታለን።

ቢቢሲ፡ ከዚህ በፊት አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ቁርጥ ሥጋ በጣም እንደሚወዱ ተናግረው ነበር። በአውደ ዓመት ላይ ቁርጥ ሥጋ እንዴት ነዎት?

አቶ ኃይለማሪያም፡ አዎ በተገኘ መጠን ቁርጥ ሥጋ እመገባለሁ። በርግጥ ውፍረትን ለመቀነስም ሆነ ጤናማ የምግብ ሥርዓት ለመከተል ጭምር እንደ ሥጋ ያሉ ፕሮቲኖች ይመከራሉ።

ከመጠን በላይ ሆነው ወደ ዩሪክ አሲድ እንዳይቀየሩ ጥንቃቄ ከተደረገ ማለት ነው። ከልጆቼም አንዷ በጣም ትወዳለች።

ቢቢሲ፡ ስለዚህ በዓመት በዓል ወቅት ጥሬ ሥጋ ከቤታችሁ አይጠፋም?

አቶ ኃይለማሪያም፡ አይጠፋም!

ቢቢሲ፡ ለአዲስ ዓመት ለቤተሰብ ስጦታ መስጠት ላይ እንዴት ነዎት?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ በአውደ ዓመት እንኳን ብዙም ስጦታ በባሕላችንም አልተለመደም። ምናልባት ፖስት ካርድ ካልሆነ።

ነገር ግን በተለያየ ጊዜ ስጦታ እንሰጣጣለን። ለእኛም ስጦታ ይመጣልናል።

ከሚመጡልን ስጦታዎች መካከል አበባ፣ በግ እና መጠጦች ይገኛሉ። ነገር ግን እኛ መጠጥ ስለማንጠጣ አጠራቅመን ሸጠን ለሌላ ዓላማ እናውለዋለን።

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢቢሲ፡ በአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ስጋትዎት ምንድን ነው?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ እኔ ሁልግዜ ተስፋዬ በእግዚአብሔር ላይ ነው። በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ መቼም ተስፋ አልቆርጥም። መልካም ነገር ያደርጋል ብዬ አምናለሁ።

ስጋት እና ተስፋ ግን የሰው ልጅ ዕለት ተቀን የሚፈራረቁበት ጉዳዮች ናቸው። ከእነሱ ውጪ ሆኖ መኖር የሚችል ሰው የለም። አንዳንዴ ተስፋ ያይላል አንዳንዴ ስጋት ያይላል።

በአገራችንም ሆነ በግል ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ በዚያው ልክም ስጋት የሚያጭሩ፣ መፍታት ሲገባን ያልፈታናቸው የተጠራቀሙ ችግሮች አሉ።

እነዚያን ከስሜት በጸዳ፣ በሰከነ ሁኔታ፣ አርቆ በማሰብ እንደዚሁም ፍቅርን ሰላምን እና መተሳሰብን ማዕከል አድርጎ ጥላቻን እና ምሬትን መፍታት ያስፈልጋል።

በርካታ አገራት ብዙ ስጋቶች በተፈጠሩባቸው ጊዜ ያንን ትምህርት አድርገው ከእንግዲህ በቃኝ የሚሉበት ወቅት አለ። የአውሮፓ አገራት ሲመሰረቱ በብዙ ጣጣዎች ውስጥ አልፈው ነበር፤ ግን ያንን በቃን ብለው ነው ያመለጡት።

እኛም አሁን ባለንበት ሁኔታ በቃን፣ ሰለቸን ከዚህ በኋላ አይደገም ብሎ ሕዝቡ በምሬት ያንን የሚስማማበት ወቅት እየደረሰ ይሆን? በሁሉም አቅጣጫ ያሉ መሪዎች የሚስማሙበት ጊዜ እየደረሰ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ።

ይህ ከሆነ ያለፈውን ለታሪክ አስቀምጦ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሸጋገር እድል አለ። ያ ካልሆነ ወደ ጥፋት የመሸጋገር ዕድል ይኖረዋል።

ለእኔ ግን ተስፋዬ 'ይህ በቃን' ብለን ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ይሆናል የሚል ነው።

ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ አሁን ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ይታወቃል። ይህንን ለማሻሻል ምን ሚና ይጫወታሉ?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ የእኔ ሚና ትልቅ ነው ብዬ ባልወስድም በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ አገር እንደመራ ሰው ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ጥረቶችን አደርጋለሁ።

የሰላም፣ የመተባበር እና የፍቅር መንፈስ እንጂ የጥላቻ እና የጥሎ ማለፍ ስሜት የሚመራው እንዳይሆን ለማሳሰብ እና ለመምከር እሞክራለሁ።

ይሄ በቃል ይባላል እንጂ በተግባር ሲተገበር ከባድ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ ተጸዕኖ ማሳደር የሚችሉ ሰዎችን አገኛለሁ። በተለይም አፍሪካዊያን እና ምዕራባዊያን መሪዎችን በማግኘት ትክክለኛውን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ለማብራራት እሞክራለሁ። አገሪቱ ካለችበት ችግር እንድትወጣ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት አደርጋለሁ።

ያልተረዱት እውነታ ካለም ለማስረዳት እና በተለይም ደግሞ ትኩረታቸው ተፋላሚ ወገኖች ላይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንዲሆን ለማድረግ እሞክራለሁ።

ሕዝቡ ላይ ትኩረታቸውን ካላደረጉ ተፋላሚ ወገኖች በሚፈጥሩት ችግር ሕዝቡ ከፍተኛ ቅጣት እንዲደርስበት ይሆናል።

ያ እንዳይሆን ሁሌም ሕዝቡን እንዲመለከቱ እና መንግሥታትንም እንዲመክሩ፤ ከሚያባብስ ነገር ይልቅ የሚያግባባ ነገር እንዲያደርጉ እመክራለሁ።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ከስቃይ የሚያስወጣ እንጂ ስቃዩን የሚያበዛ እርምጃ እንዳይወስዱ አሳስባቸዋለሁ።

በተለይም ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ አገር መሰረቷ የተናጋ እንደሆነ መላው አፍሪካ፣ ብሎም መካከለኛው ምሥራቅም ሆነ የአውሮፓ አገራት ድረስ የሚደርስ ቀውስ እንደሚመጣ አውቀው የተረጋጋ ፖሊሲ እንዲይዙ ጥረት አደርጋለሁ።

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከቤተሰቦቻቸው ጋር

ቢቢሲ፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ በርካቶች ወደኋላ ሄደው ልጅነታቸውን ያስባሉ። እርስዎ አዲስ ዓመት ሲመጣ ወደ አዕምሮዎት የሚመጡ ትዝታዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ በተለይም አንድ መጥፎ ትዝታ አለኝ። ልክ 12ኛ ክፍል እንደጨረስኩ በነሐሴ ወር መጨረሻ ነበር አባቴ ሕይወቱ ያለፈው።

አዲሱ ዓመት በለቅሶ ላይ ሳለን ነበር የደረሰው። ዩኒቨርሲቲም መግቢያ ወቅት ነበር እና ከለቅሶ እንደተነሳሁ ነበር ለምዝገባ የሄድኩት። ያ አዲስ ዓመት ለእኔ የከፋ አዲስ ዓመት ነበር። እሱን ሁልጊዜ ነው የማስታውሰው።

አባታችን ለእኛ ሁሉም ነገር ስለነበረ ያ ስብራት የነበረ አዲስ ዓመት አልረሳውም። በሌላ በኩል ደግሞ ከባለቤቴ ጋር ሠርጋችን በነሐሴ መጨረሻ ላይ ነበር። እና በወጣትነት በአዲስ ዓመት ያሳለፍነው ሁልጊዜም ትዝ የሚለን መልካም ትዝታችን ነው። እና ሁለቱም ነገሮች ተፈራርቀው አይቻለሁ።

ከዚያ በተረፈ ግን በእኛ አካባቢ በልጅነታችን አሁን በተለምዶ መስቀል የሚባለው ዓመት በዓል አለ። በእርግጥ በብሔሩ አጠራር 'ጊፋታ' ነው የሚባለው፤ ኋላ ከመስቀል ጋር ተገጣጠመ እንጂ። የዘመን መለወጫ ነው። መስከረም 17 ከሚውልበት ሳምንት ጀምሮ ለወራት ነው የሚከበረው።

ያንን በጣም ከልቤ ያከበርኩበት ጊዜ ነው፤ እስከ 15 ዓመቴ ድረስ። ከዚያ በኋላ እሱም በተለያየ ምክንያት እየቀዘቀዘ መጥቷል።

ቢቢሲ፡ ምንም አንኳን በአውደ ዓመት ዙሪያ ቢሆንም ቆይታችን ለማሳረጊያ አንድ ጥያቄ ላንሳ። ራስዎን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ካገለሉ በኋላ፣ ለኢትዮጵያ ይመጣል ብለው ያሰቡት ለውጥ መጥቷል ብለው ያምናሉ?

አቶ ኃይለማሪያም ፡ የእኔ ራሴን ከሥልጣን ማግለል በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት እና ስጋት በማርገብ እና ሕዝቡ ተስፋ እንዲሰንቅ በማድረግ የራሱን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ከሥልጣን ወርዶ በሰላም የኖረ ሰው በአገራችን ባልነበረበት ሁኔታ ይህ እንደሚቻል አንድ ተምሳሌት መፈጠሩ አንድ ነገር ነው።

እኔም የታደልኩ ነኝ ብዬ አምናለሁ። ይሄ በሁሉም መስክ የሚያስተላልፈው የራሱ መልዕክት አለው።

አሁን በአመራር ላሉትም ይህ እንደሚቻል አሳይቷል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይም "ልክ እንዳንተ ዕድል ቢገጥመኝ እና እኔም በጊዜዬ አስረክቤ በሰላም ከሕዝቡ ጋራ የምኖርበት ሁኔታ ቢፈጠርልኝ" ሲል ሰምተሽ ይሆናል።

ከእኔ በኋላ ያሉ መሪዎች ሥልጣን የመጨረሻው ሕይወት እንዳልሆነ እና ከሥልጣን ወርዶ መኖር እንደሚቻል ያሳየ ነው ብዬ አስባለሁ። እንዲያውም የተሻለ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል ያሳያል። ምንም እንኳን አስተዋጽኦ የምናደርገበት መንገድ ቢለያይም።

ነገር ግን የአገራችን የኢትዮጵያ ችግር በጣም ጥልቅ ነው። በእኔ ወይም በአንድ ሰው ከሥልጣን መውረድ የሚፈታ አይደለም።

የተወሰነ የራሱን መደላድል የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። እኔ አሁን ወጥቼም ቢሆን ሳስበው የአገራችን ችግር ጥልቀቱን ባለመረዳት ብዙ እንጎዳለን።

ኢትዮጵያ መግለጽ ከምችለው በላይ እጅግ የተወሳሰበ፣ የተደራረበ፣ እጅግ በጣም የቆየ፣ እንዲሁም አሁን የተፈጠሩ ችግሮች ውስጥ ያለች አገር ነገር ነች።

ይሄ መፍትሄው እና መፍቻው ምንድን ነው ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ሌላው ቀርቶ አሁን ያለው አመራር ሁሉ ወረድኩ ቢል እንኳን የሚፈታ አይደለም። ችግሩ ከአመራር መለዋወጥ በላይ ነው።

ይልቁንም አንድ ከፍተኛ የሥርዓት ለውጥ ይጠይቃል። በርካታ ቅሬታ እና ቁርሾ የሞላው ሕብረተሰብ ነው ያለን።

ወጣቱ የራሱ አስተሳሰብ አለው፤ የቆየው ሰው የራሱ አሰተሳሰብ አለው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጣም ብዙ ምልክቶች አሳርፈው ያለፉ ትውልዶች አሉ።

በእኛ አጠራር የ1960ዎቹ ትውልድ አሁንም በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ ሆኖ እስካሁን ለሥልጣን እየተፎካከሩ ያሉ ሰዎችም ያሉበት ማለት ነው።

ይሄ ትውልድ በወቅቱ የያዛቸው አቋሞች ኢትዮጵያን በመልካምም ሆነ በመጥፎው ጠባሳ ጥለው ያለፉ ናቸው።

ከእነዚያ ውስጥ አንዱ የብሔር ጥያቄ የተመለሰበት መንገድ ነው። አሁን በደንብ እንደገባን ሁላችንም እንዳሰብነው የብሔሮችን መብት እና እኩልነት ከማምጣት አልፎ የመጠፋፊያ መንገድ ብሎም የጽንፈኝነት አዝማሚያ እያሳየ ነው።

ከዚህ የተነሳ ብዙ መከራ ውስጥ ነው ያለነው። ይህንን በግልጽ ተወያይተን መካከለኛውን መንገድ መፈለግ አለብን።

ከጽንፈኝነት የራቀ ነገር ግን የሃይማኖት እና የብሔር መብቶችን ጨምሮ የቡድን መብቶች ከዜግነት መብት በማይበልጡበት መንገድ መፍቻ አማራጮችን ቁጭ ብለን መፈለግ አለብን።

ይህ በተለያየ መንገድ የተመሰረቱ እንደ ሶቪየት ኅብረት ያሉ አገራት በሚፈጠሩበት ጊዜ የመጣ ሃሳብ ነው። ኋላ ወደ ራሳችን ስናመጣው ሕዝባችን የተቀላቀለ መሆኑን በሚረሳ መንገድ ነበር ያስገባነው።

እያንዳንዱ ብሔር ወጥ ነው ብለን በማሰብ ያስገባነው ነገር አሁን መላወሻ አሳጥቶናል። እንግዲህ እንደዚህ አይነት እና መሰል ያልተፈቱ ጥያቄዎች አሉ።

የጋራ ፍቺ ለመስጠት የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸውን በሙሉ ያሳተፈ ውይይት ተደርጎ ለእነዚህ ችግሮች መፍተሄ ማፈላለግ ያስፈልጋል።

ለምሳሌ የእኔን ብሔር ወስደሽ ወላይታዎች በአጼ ምኒሊክ አገር የመመስረት ሂደት ውስጥ ተጨፍልቀናለን፣ በመቶ ሺዎች ተጨፍጭፈናል ብለው እስካሁን ይናገራሉ። እውነት ነው፤ ይሄ አልተደረገም አልልም።

ነገር ግን ከአንድ ፊውዳል ንጉሥ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ የምናስብ ከሆነ ከታሪክ ጋር ግጭት እንገባለን። በወቅቱ ንጉሥ ጦናም ቢሆኑ ይሄንን ዕድል ቢያገኙ ንጉሥ ምኒሊክ ያደረጉትን ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ ነው የማምነው።

ንጉሥ ጦናም በራሱ አካካቢ የፊውዳል ሥርዓት ጫና ፈጥሯል። ስለዚህ ሁሉም የፊውዳል ሥርዓቶች የሚፈጽሙት ነገር ነው። ነገር ግን ልክ አልነበረም።

ያንን ቁርሾ ይዞ እርሳቸው የተፈጠሩበትን ጭቁኑ የአማራ ብሔር ይሄንን ችግር እንደፈጠረ ተደርጎ የሚሳልበት እና የተለያየ ስያሜ የሚሰጥበት መንገድ መፈታት አለበት።

ይሄ አሁን ባለንበት ሁኔታ ያልተፈታ ቁርሾ ጥሎ ንጹሁ ሕዝብ እንዲጎዳ እና እንዲሞት ያደርጋል። የአገራችንን የበፊት ታሪክ በጎውን ይዘን፣ ሌላውን ደግሞ ሁለተኛ በማይደገምበት ሁኔታ እንዴት ነው መሻገር የሚቻለው የሚለው ላይ መስራት አለብን።

ሁሉም የራሱን ያልሻረ ቁስል ተንፍሶ እና አንዳንዱን ደግሞ ልክ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ላይ ተስማምቶ ማለፍን ይጠይቃል። ጥልቅ እና አካታች የማኅበረሰብ ውይይት እና መግባባት መፈጠር አለበት። ይሄ ካልሆነ ግን ስጋታችን የበለጠ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።

እናም የእኔ መውጣት ሁሉን ነገር የሚፈታ አይደለም። በወቅቱ የተወሰነ ተስፋ ጭሮ ነበር። ያ ተስፋ በሂደት እየቀዘቀዘ እና እየቀነሰ መምጣቱን ሁላችንም የምናየው ነገር ነው። ነገር ግን ወደ ትክክለኛው መንገድ እንድንገባ አሁንም ዕድል አለን።