ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ በተቃጣ የሚሳዔል ጥቃት ወታደሮች ተጎዱ
በምዕራባዊው የኢራቅ ክፍል በሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ ላይ በተቃጣ የሚሳዔል ጥቃት ወታደሮች ጉዳት ደረሰባቸው።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጠው በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች አል አሳድ አየር ማረፊያን ዒላማ አድርገው ባለስቲክ ሚሳዔሎችና ሮኬቶች ተኩሰዋል።
አየር ማረፊያው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ሲሆን ጥቃቱ የተሰነዘረው ቅዳሜ ጥዋት ነው።
ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የዩኤስ ወታደሮች “በደረሰባቸው ‘ትራውማቲክ የአዕምሮ ጉዳት” ምክንያት ሕክምና እያገኙ ነው።
ቢያንስ አንድ የኢራቅ ወታደር በጥቃቱ መጎዳቱም ተዘግቧል።
ኢስላሚክ ሬዚስታንስ ኢን ኢራቅ እያለ ራሱን የሚጠራው ሚሊሻ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።
ዋሺንግተን ኢንስቲትዩት ኦፍ ኒር ኢስት ፖሊሲ የተሰኘው ተቋም ይህ ቡድን ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መገባደጃ ገደማ ብቅ ያለ እንደሆነ ይገልጣል።
ተቋሙ ጨምሮ ይህ ቅንጅት የተለያዩ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ጥምረት ነው ይላል።
በተለይ በቅርብ ሳምንታት ሌሎች የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ኃላፊነት ሲወስድ ይደመጣል።
አል አሳድ አየር ማረፊያ በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስባቸው የአሜሪካ ጦር መቀመጫዎች መካከል አንዱ ነው።
የአሜሪካ ጦር ኃይል እንደሚለው በርካታ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን ሳይመቱ እንዲመክኑ ቢደረጉም የተወሰኑ ሚሳዔሎች ግን ይህን አልፈው ጣቢያውን መትተዋል።
ባለፈው ጥቅምት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ግጭት ከተጀመረ ወዲህ በሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ጥቃት በርክቷል።
አሜሪካ ጥቃቱን የሚሰነዝሩት ሚሊሻዎች በኢራን የሚደገፉ ናቸው ብላ ታምናለች።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በተለይ በቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ ንግድን አስተጓጉለዋል ባሏቸው የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ላይ በቅርብ ሳምንታት ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።
ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካ ጦር አብዛኛውን የመንን በሚቆጣጠረው የሁቲ አማፂ ቡድን ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተሰምቷል።
የኢራን ጦር በበኩሉ በቅርብ ቀናት ሶሪያ፣ ኢራቅ እና ፓኪስታን በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የሚሳዔል ጥቃት ማድረጉ ይታወሳል።
ቅዳሜ ዕለት ኢራን በሶሪያ መዲና ደማስቆ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት አምስት ነባር የፀጥታ አባላቴን ገድላብኛለች ስትል ወቅሳለች።