ፓኪስታን እና ኢራንን ጦር ያማዘዘው ምንድን ነው? ውጥረቱስ ወዴት ያመራ ይሆን?

ከቀናት በፊት ፓኪስታን በኢራን የሚገኙ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን ተከትሎ 9 ሰዎች ተገድለው ነበር።

ጥቃቱን በተመለከተ የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብዙ ጥናት የተደረገበት በኢራን የታጣቂዎች መደበቂያ የሆነ ቦታ ነው ዒላማ የተደረገው ብሏል።

ከዚህ የአየር ጥቃት በኋላ ኢራን በተራዋ በፓኪስታን የመሸጉ ናቸው ያለቻቸውን ታጣቂዎች ዒላማ አድርጋ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

በዚህ ጥቃት ሁለት ሕጻናት መገደላቸውን የፓኪስታን መንግሥት አስታውቋል።

ሁለቱም መንግሥታት በእነዚህ ጥቃቶች ደስተኞች አይደሉም። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውንም እስከማቋረጥ ደርሰው ነበር።

ፓኪስታን በኢራን ተደብቅው ይገኛሉ በምትላቸው ተገንጣይ ቡድኖች ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች።

ኢራን ደግሞ በፓኪስታን መቀመጫውን ባደረገው የሱኒ ታጣቂ የሆነው ጃኢሽ አል-አደለ የተባለውን ቡድን ዒላማ አድርጋለች።

ስለ ፓኪስታን ጥቃት ምን ይታወቃል?

የፓኪስታን መንግሥት በአገሩ ውስጥ የሽብር ተግባራትን ፈጽመዋል ያላቸውን የባሎቺስታን ነጻነት ሠራዊት እና የባሎቺስታን ነጻነት ግንባር ኢራን ውስጥ መምታቱን ይገልጻል።

የፓኪስታን ጦር እነዚህን ሁለት ቡድኖች ለመምታት ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ሮኬቶች፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይገልጻል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ኢራን እና ፓኪስታን ድንበር ላይ የምትገኘው አዋሳኟ የኢራን ከተማ ሳራቫን አቅራቢያ ነው።

የባሎቺስታን ታጣቂ ቡድኖች እነማን ናቸው?

ለበርካታ አስርት ዓመታት በፓኪስታኗ ባሎቺስታን ግዛት በርካታ ተገንጣይ ኃይሎች የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እነዚህ ቡድኖች በፓኪስታን ጦር እና ፖሊስ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችም ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

ከተገንጣይ ቡድኖቹ መካከል ጠንካራዎቹ የባሎቺስታን ነጻነት ሠራዊት እና የባሎቺስታን ነጻነት ግንባር ናቸው። የባሎቺስታን ነጻነት ሠራዊት በበሺር ዜብ የሚመራ ሲሆን፣ የባሎቺስታን ነጻነት ግንባር ደግሞ በዶ/ር አላህ ናዛር ባሎች ይመራል።

የፓኪስታን ባለሥልጣናት የእነዚህ አማጺያን ቡድኖች አባላት በኢራን ተሸሽገው እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል በማለት ቴህራንን ይከሳሉ።

እነዚህ የፓኪስታን ግዛት ተገንጣይ ቡድኖች ነጻነትን የሚጠይቅ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር።

የተንገንጣይ ቡድኖቹ እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ የባሎቺስታን ነጻነት ሠራዊት እንቅስቃሴ በቀድሞው የፓኪስታን ፕሬዝዳንት ፔርቬዝ ሙሻራፍ ዘመን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የፓኪስታን መንግሥትም ይህን ቡድን እአአ 2006 ላይ በጥቁር መዝገብ ላይ ስሙን አስፍሮት እርምጃ ሲወስድበት ቆይቷል።

ይህ ቡድን የቻይና-ፓኪስታን የኢኮኖሚ ኮሪዶር ፕሮጀክትን በመቃወም ቻይናውያንን እና የቻይና ተቋማትን ዒላማ ማድረግ ሲጀምር የዓለምን ትኩረት መሳብ ችሎ ነበር።

እአአ 2018 ላይ ቡድኑ ቻይናውያን ሠራተኞችን በያዘ አውቶቡስ ላይ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢፈጽምም በጥቃቱ ሕይወቱ ያለፈው የአማጺው ቡድን አባል ብቻ ነበር።

ኢራን በበኩሏ በመንግሥቷ ላይ ነፍጥ ያነሳውን ጃኢሻ አል-አደለ (የፍትሕ እና ነጻነት ሠራዊት) ቡድንን ለመምታት ነበር በፓኪስታን ግዛት ውስጥ የአየር ጥቃት የፈጸመችው።

ይህ ቡድን የብዙሃን ሺዓዎች አገር በሆነችው ኢራን ለሚኖሩ ሱኒዎች የመብት ተሟጋች ነኝ ሲል እራሱን ይገልጻል።

ሺዓ ሙስሊሞች በሚበዙባት ኢራን ይህ ቡድን በርካታ ጥቃቶች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ በመፈጸም ክስ ይቀርብበታል።

ይህ ቡድን እአአ 2005 ላይ በወቅቱ የኢራን ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አሕመዲነጃድ ላይ ያልተሳካ ጥቃት ፈጽሞ ነበር።

ኢራን ጃኢሽ አል-አደለ የአሜሪካ እና የእስራኤል ድጋፍ አለው ስትል ትከሳለች።

እአአ 2009 ላይ ኢራን የዚህን ቡድን የሚሊሻ ቡድን ኃላፊ የሆነውን አብዶልማሌክ ሪጊ በቁጥጥር ሥር አውላ በቦምብ ጥቃቶች እንዲሁም የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ሰላይ የሚል ክስ አቅርባ በስቅላት ቀጥታዋለች።

አሁን እየሆነ ያለው ምንድን ነው?

የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮችን በቅርበት የሚከታተሉት ሳይድ ሞሐመድ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ ኢራን ከውስጥም ከውጪም ያለባትን ጫና ትኩረት ለማስቀየር ነው ቡድኑን ዒላማ ያደረገችው ይላሉ።

እንደተንታኙ ከሆነ የኢራን መንግሥት በአገር ውስጥ ጉዳይ ተወጥሮ ተይዟል። ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ባላት ተሳትፎ ደግሞ ባላንጣ ከምትላቸው ምዕራባውያን እንዲሁም አጋር ከምትላቸው ሐማስ፣ ሄዝቦላህ እና ሁቲዎች ጫናዎች አሉባት።

ኢራን እስካሁን ድረስ በኢራቅ፣ በሶሪያ እና በፓኪስታን ጥቃቶችን ያደረሰችው በውስጣዊ አገራዊ ጉዳዮቿ ትኩረት እንዳያገኙ ነው ይላሉ ተንታኙ።

በዋሽንግተን የኒው ላይንስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ስትራቴጂ ኤንደ ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ካምራን ቡካህሪ ደግሞ ፓኪስታን ለኢራን ጥቃት ምላሽ የሰጠችው ቴህራን ኢራቅ ላይ እንዳደረገችው ደጋግማ የአየር ጥቃት እንዳትፈጽም ነው ይላሉ።

ባለሙያው በኢራን እና በፓኪስታን አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች የተሰባሰቡ ቡድኖች ለሁለቱም አገራት ችግር ፈጣሪ ሆነው ቆይተዋል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ኢራን ዒላማ ያደረገችው ቡድን በፓኪስታን ዘንድም እንደ ጠላት የሚታይ ነው።

በቀጣይ ምን ይፈጠራል?

ፓኪስታናዊው ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ባቂር ሳጃድ ምንም እንኳ አሁን ላይ የአየር ጥቃቶች ቆመው ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን መልሰው ቢያስቀጥሉም፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት መቀጠሉ አይቀሬ ነው ይላል።

“በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ድንገት ይቀንሳል ማለት አይደለም። በአገራቱ መካከል ያለው አለመተማመን በአማጺያኑ ተደጋጋሚ ጥቃት ተጋግሎ በቀጠናው ያለውን የደኅንነት ስጋት ከፍ ያደርገዋል” ይላል።