ቱርክ የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄን አጸደቀች

የፊንላንድ ፕሬዚደንት ሳውሊ ኒኒስቶ እና የቱርኩ ፕሬዚደንት ኤርዶዋን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቱርክ ምክር ቤት ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ አጸደቀ።

በዚህም ፊንላንድ የኔቶ 31ኛ አባል አገር ትሆናለች።

ፊንላንድ የምዕራቡን የመከላከያ ጥምረት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ "ሽብርተኞችን ትደግፋለች" በሚል ምክያት ቱርክ ለወራት ሳትቀበል ቆይታ ነበር።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርባ የነበረችው ስዊድን ላይም ተመሳሳይ ክስ ያቀረበች ሲሆን አንካራ እስካሁን የስቶኮልም ጥያቄን አልተቀበለችም።

አንድ አገር ኔቶን ለመቀላቀል የሁሉንም አባል አገራት ድጋፍ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

በመሆኑም ፊንላንድ ስትጠብቅ የነበረውን የአንካራን ድጋፍ በማግኘቷ በመጪው ሐምሌ ወር በሉቱዌኒያ በሚካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ስብስቡን በይፋ ትቀላቀላለች።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲብ ታይፕ ኤርዶዋን በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ለፊንላንድ ድጋፋቸውን የገለጹ ሲሆን አገሪቷ ለቱርክ ደኅንነት የወሰደችውን "ትክክለኛ እና ተጨባጭ" እርምጃዎች አድንቀዋል።

ይሁን እንጅ ለስዊድን ያላቸው አቋም አሁንም ግልጽ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ስዊድን የኩርድ ታጣቂዎችን ትደግፋለች እንዲሁም በስቶኮልም ጎዳና ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ፈቅዳለች ሲሉ በድጋሜ ከሰዋል።

ሁለቱ የሰሜን አውሮፓ አገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለፈፀመችው ወረራ ምላሽ ለመስጠት የራሳቸውን ወታደራዊ ገለልተኝነት ትተዋል።

በአንድ ምሽትም የኔቶ አባልነት ድጋፍ ዝቅተኛ ከነበረው የፊላንዳውያን አንድ ሦስተኛ ድጋፍ ወደ 80 በመቶ ከፍ ብሏል።

ሩሲያ ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ስትቃወምና ስታስጠነቅቅ መቆየቷ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ አገሪቷ የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም አሳስበው ገለልተኛ መሆኗን ማቆሟም ትልቅ ስህተት እንደሚሆን ተናግረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም የአገሪቷ ውሳኔ ከባድ ምላሽ እንደሚያስከትል ያስጠነቀቁ ሲሆን በትክክል ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ ግን አልገለጹም።