ከአሜሪካው ኤምአይቲ ዩኒቨርሲቲ መጥተው ለኢትዮጵያውያን ‘አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ’ ያስተማሩት ወጣቶች

ዮዋና ቱሩራ በዓለም ታዋቂው የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተማሪ ናት።

ዮዋና፤ በቅርቡ ብራይተር ጄኔሬሽን በተሰኘው የሥልጠና ፕሮግራም አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለታዳጊዎች ሥልጠና ከሰጡ ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት።

እሷ እና ሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኤምአይቲ ተማሪዎች ካለፈው የፈረንጆቹ ወር ጀምሮ ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ለመጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት ሰጥተዋል።

“ለተማሪዎች ስለ ‘ፓይተን ፕሮግራሚንግ’ ሥልጠና እየሰጠን ነው” ትላለች ዮዋና።

ዮዋና እና ጓደኞቿ ከጥር 16 እስከ መጋቢት 4/2023 የሚቆይ ሥልጠና ሰጥተዋል።

ተማሪዎች የክረምት እረፍታቸውን ተጠቅመው በግዙፉ ዩኒቨርሲቲ የተማሩትን ለኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ሊያጋሩ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።

ብራይተር ጄኔሬሽን

ብራይተር ጄኔሬሽን በዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተቋቋመና ቀጣዩን የኢትዮጵያ ትውልድ ለማበልፀግ ሥልጠና የሚሰጥ ፕሮግራም ነው።

የፕሮግራሙ መሥራቾች ሳይንቲስቶቹ ብርሃን ቡልቻ (ዶ/ር) እና ፀጋ ሰለሞን (ዶ/ር) ናቸው።

ሁለቱ ሳይንቲስቶች በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 2021 ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አቅንተው ሳለ ባዩት ሁኔታ ተነሳስተው ይህን ፕሮግራም እንዳቋቋሙ ብርሃኑ ቡልቻ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

“እኛ ምን ማድረግ እንችላለን ብለን እንድንጠይቅ አደረገን። የእኛ አስተዋፅዖ ብዙ ባይሄድ እንኳ ሌሎችን ማሳተፍ አለብን ብለን የጀመርነው ነው።”

በሁሉም ክፍለ ዓለማት ያሉ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን መርዳት ይፈልጋሉ የሚሉት ብርሃኑ፣ ነገር ግን ገንዘብ ከመላክ ባለፈው መሰል እርዳታ የሚያደርጉበት ብዙ አማራጭ እንደሌለ ይገልጣሉ።

የናሳ ሳይንቲስቱ እንደሚሉት ‘ሰከንድ ጀኔሬሽን’ የሚባሉት በውጭ አገር ተወልደው ያደጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የግላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።

ነገር ግን ይህ እንዲሆን ብዙ አማራጭ ማዘጋጀት እንደሚያሻ ያስረዳሉ።

“ዳያስፖራው የሚቀጥለውን የኢትዮጵያ ትውልድ የሚረዳበት መድረክ ብዙ የተመቻቸ አይደለም።”

ብራይተር ጄኔሬሽን ሁለት ዓይነት የሥልጠና አማራጮችን ያቀፈ ነው። ‘ቨርቹዋል’ (በበይነ መረብ አማካይነት) እና በአካል የሚሰጥ ሥልጠና።

“ቨርቹዋል ማለት አንድ ሰው የትኛውም የዓለም ጫፍ ሆኖ ኢትዮጵያ ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተምርበት መንገድ ነው። ከኢትዮቴሌኮም ጋር በገባነው ስምምነት መሠረት ኩባንያው ያቀረበልንን ብሮድባንድ በመጠቀም እናስተምራለን።”

ሁለተኛው የሥልጠና ፕሮግራም በአካል በመገኘት የሚሰጥ ሲሆን፣ ዮዋና እና የኤምአይቲ ጓደኛቸው በዚህኛው ፕሮግራም ነው አዲስ አበባ የመጡት።

የኮምፒውተር ቋንቋ

ዮዋና ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው።

“በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ካደግኩበት አካባቢ በጣም የተለየ ሕይወት ነው ያለው እዚህ። በጣም ደስ ይላል።”

ዮዋና፤ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተመረጡ ተማሪዎች ‘ፓይተን’ የተሰኘውን የኮምፒውተር ቋንቋ አስተምራለች።

“ያስተማርናቸው የኮምፒውተር ቋንቋ ነው። የኮምፒውተር ቋንቋ ተጠቅሞ እንዴት ችግርን መፍታት ይቻላል የሚለውን በተግባር አስተምረናቸዋል።”

ዮዋና፤ ታዳጊዎቹ ትምህርት ቤት የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር የሚለውጡበት ብዙ አማራጭ እንደሌላቸው አስተውላለች።

ምንም እንኳ የኮምፒውተር ቋንቋ ማስተማር ቀላል ባይሆንም፣ ተማሪዎቹ ከቀን ወደ ቀን የሚገርም ማሻሻል እንዳመጡ ትናገራለች።

ዮዋና እና ጓደኞቿ ከኮምፒውተር ቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች የኮምፒውተር ክህሎቶችን አስተምረዋል።

“ለፕሮጀክት እንዴት ‘ፕሮፖዛል’ መፃፍ ይቻላል? ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዴት ‘ኮሚዩኒኬት’ ማድረግ ይችላሉ? የሥራ ሥነ-ምግባር እንዴት ያዳብራሉ? ለችግሮች መፍትሔ እንዴት ማበጀት ይቻላል? የመሳሰሉ ትምህርቶችን ሰጥተናል።”

“የምናስተምራቸው ትምህርት ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለማኅረሰባቸውም የሚጠቅም እንዲሆን እንፈልጋለን” የምትለው ዮዋና ተማሪዎቹም አቀባበላቸው በጣም ጥሩ እንደነበር ትናገራለች።

ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ ይህ ፕሮግራም ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኮሌጅ ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሥልጠና የሚሰጡበት ብቻ ሳይሆን ስለአገራቸው ዕውቀት ቀስመው የሚመለሱበት እንዲሆን ነው ምኞታቸው።

ተማሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ 130 የተመረጡ ተማሪዎችን በፈረንጆቹ ከጥር 16 እስከ መጋቢት 4 ድረስ ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል።

የወደፊት ዕቅድ

አዲስ አበባ መጥተው ሥልጠና የሰጡት የኤምአይቲ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ሰውተው እንደመጡ ያስረዳሉ።

“በጣም የተጨናነቀ ጊዜ ያላቸው ናቸው። አገራችን እናገልግል ብለው ሲመጡ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች አገርን ማገልገል ከእነሱ ይማራሉ ብለን እናምናለን” ይላሉ።

ሥልጠናውን ለማዘጋጀት ለአራት ወራት ያክል ዝግጅት እንደተደረገ የሚናገሩት ሳይንቲስቱ ለእያንዳንዱ ተማሪ ቃለ-መጠይቅ ተደርጎ እንደተመረጡ ይናገራሉ።

“የመረጥናቸው ተማሪዎች 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ለዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጁ ነው። እርግጥ አንዳንዶቹ ፍላጎታቸውን ላያውቁት ይችላሉ። የኤምአይቲ ተማሪዎች ያላቸውን ልምድ ሲያጋሩ ከትምህርት ባለፈ መነቃቃትን እንደሚፈጥሩ እምነት አለኝ።”

ዮዋና፤ በርካታ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተማሪዎች በተመሳሳይ ለታዳጊዎች ሥልጠና የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ትናገራለች።

“ይህ ፕሮግራም የበለጠ አድጎ በሚቀጥሉት ዓመታት የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲያካትት ነው የምንፈልገው” ትላለች።

አብዛኛዎቹ ተማሪዎቹ ቤታቸው ውስጥ የበይነ-መረብ አልያም የኮምፒውተር አቅርቦት ስላማይኖራቸው ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ መማር ቀላል እንደማይሆንላቸው ትረዳለች።

“ወደፊት ከተሳካልን ተማሪዎች መጥተው እነዚህን አገልግሎቶች የሚያገኙበት ማዕከል መፍጠር እንፈልጋለን።”

ብርሃኑ ቡልቻ (ዶ/ር) ቀጥሎ ከሃርቫርድ፣ ስታምፈርድ እና ሌሎችም ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያስተምሩ የሚደርግበት ፕሮግራም እንደሚሰናዳ ይገልጣሉ።

የብራይተር ጄኔሬሽን መሥራቹ፤ የሚቀጥለው ፕሮግራማቸው በኢትዮጵያ ክረምት የሚጀመር ‘ቨርቹዋል’ ሥልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በአፋር፣ በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ፣ በደብረ ብርሃን. . . በአጠቃላይ በዘጠኝ ማዕከላት ‘ቨርቹዋል’ ሥልጠና ሰጥተናል። በሚቀጥለው ይህን ወደ 50 አሊያም 60 ማዕከላት በማስፋፋት ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት እንጀምራለን።”