ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች “ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማስቻል” የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ
የኢትዮጵያ መንግሥት ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች "ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ ለማስቻል" ብሄራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ።
ይህ ውሳኔ የተደረሰው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህዳር 3፣ 2015 ዓ.ም ባካሄደው 15 መደበኛ ስብሰባ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው "ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግም" ይህ ኮሚሽን እንዲቋቋም ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም “በአገሪቱ የልማት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስቻልም" የኮሚሽኑ አስፈላጊ እንደሆነም ህዳር 3፣ 2015 ዓ.ም የወጣው መግለጫ አትቷል።
በዚህም መሰረት ይህንን ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ ደንብንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀ ሲሆን ይህ ደንብ ከጸደቀበት ዕለት ጀምሮም በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑም ተገልጿል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ጦርነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨትና የመጨረሻ እልባት እንዲበጅላቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም በዚህ መግለጫ ተጠቅሷል።
የትናንትናው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተጨማሪ በመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውሳኔ አሳልፏል።
ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ በስራ ላይ ያለውን የመከላከያ የመከላከያ አዋጅ የሚተካ ነው።
ይህንንም ለመተካት እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው “ከመከላከያ ሰራዊት ወቅታዊ እና የወደፊት ግዳጆች ጋር የሚጣጣም የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ” እንደሆነም ተጠቁሟል።
“መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችል የለውጥ ስራ ላይ” እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል።
በዚህ ጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ያለው መግለጫው ይህንን ለውጥ የበለጠ ለማጎልበት እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድም ዘንድ ነውም ረቂቅ አዋጁ የቀረበው።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዲተላለፍም ወስኗል ብሏል።