የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ኬንያውያን አክቲቪስቶች "ማቀዝቀዣ ውስጥ" ታስረው እንደነበር ተናገሩ

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለመጀመርያ ጊዜ ለአምስት ሳምንታት ተሰውረው የነበሩት ኬንያውያን አክቲቪስቶች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር አመኑ።

ባለፈው ወር የዓይን እማኞች ቦብ ንጃጊ እና ኒኮላስ ኦዮኦ ጭምብል ባጠለቁ እና የፀጥታ ኃይሎችን የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች ተገድደው ወደ መኪና ውስጥ እንዲገቡ ሲደረጉ ማየታቸውን ተናግረው ነበር።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኡጋንዳ ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን ባዘጋጀው የፖለቲካ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ነው።

ቅዳሜ ዕለት ሁለቱ አክቲቪስቶች መለቀቃቸው የተገለፀ ሲሆን ባለሥልጣናት ግን በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።

ቅዳሜ ማታ በቀጥታ በተላለፈ ቃለ ምልልስ ላይ ሙሴቪኒ ሁለቱን አክቲቪስቶች "ጠብ በማነሳሳት የተካኑ ናቸው" ሲሉ ወንጅለዋቸው "ለተወሰኑ ቀናት ማቀዛቀዣ ውስጥ እንዲቀመጡ አድርገናቸዋል" ብለዋል።

ለአራት አስርት ዓመታት ሥልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ይወዳደራሉ።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ላይ በቅርቡ በጎረቤት ታንዛኒያ የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ ወጣቶች አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን ስለማሰማታቸው ተጠይቀዋል።

ሙሴቪኒ የውጭ ቡድኖችን ግጭት በመቀስቀስ የወነጀሉ ሲሆን "እዚህ ኡጋንዳ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር እናዳርጋለን የሚሉት መጨረሻቸው አያምርም" ሲሉ ዝተዋል።

ሁለቱ የኬንያ አክቲቪስቶች የተለቀቁት "የተወሰኑ የኬንያ መሪዎች" ደውለው እንዲለቀቁ በመጠየቃቸው መሆኑን ቢናገሩም ማን መሆናቸውን ግን ይፋ አላደረጉም።

ንጃጊ እና ኦዮኦ ቅዳሜ ዕለት ናይሮቢ ሲደርሱ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ንጃጊ "38 ቀናት በእገታ ስር መቆየት ቀላል አይደለም። በሕይወት እንወጣለን ብለን አስበን አናውቅም፤ ምክንያቱም የታገትነው በወታደሮች ነበር" ብሏል።

የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ግለሰቦቹ የተለቀቁት "በኬንያ እና በኡጋንዳ መካከል በተካሄደ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር" መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች እንዲለቀቁ ሲወተውት የነበረው ቮካል አፍሪካ የተባለው ድርጅት "በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ በየትኛውም ቦታ የምሥራቅ አፍሪካውያንን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ይህ ጊዜ ጠቃሚ አጋጣሚ ይሁን" ብሏል።

ቮካል አፍሪካ፣ ሎው ሶሳይቲ ኦፍ ኬንያ እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል በጋራ ባወጡት መግለጫ የኬንያን እና የኡጋንዳን መንግሥታት፣ ለግለሰቦቹ መለቀቅ የወተወቱ ዜጎችን ሁሉ አመስግነዋል።

የቀድሞው ድምጻዊ ቦቢ ዋይን፣ በሙሉ ስሙ ሮበርት ክያጉላኒ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሙሴቪኒን በመፎካከር ይሳተፋል።

ቦቢ ዋይን የኡጋንዳ መንግሥት ሁለቱ ኬንያውያን ከእርሱ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ዒላማ እንደተደረጉ ገልጿል።

"ምንም ዓይነት ጥፋት ከሰሩ ለምን ፍርድ ቤት ቀርበው በአግባቡ ክስ አልተመሰረተባቸውም?" ሲል እሁድ ዕለት በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ላይ ጠይቋል።

የኡጋንዳ የደህንነት ኤጀንሲዎች የደንብ ልብሳቸውን ሳይለብሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ይከሰሳሉ።

አልፎ አልፎ በቁጥጥር ስር የዋሉ አንዳንድ ሰዎች ችሎት ፊት ቀርበው የወንጀል ክሶች ይቀርብባቸዋል።

ሮበርት ኪያጉላኒ፤ በ2021 በተካሄደው ምርጫ 35 በመቶ ድምጽ በማግኘት የአገሪቱን 59 በመቶ ባገኙት ሙሴቬኒ ተሸንፏል።

ይሁን እንጂ ምርጫው የተጭበረበረ እና ተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ የተወሰደበት እንደነበር የሚጠቅሱ ውንጀላዎች ይቀርቡበታል።