ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለ40 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩት የ80 ዓመቱ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት በድጋሚ ለምርጫ እጩ ሆነው ቀረቡ
ለረጅም ዓመታት የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ሆነው የመሩት የ80 ዓመቱ ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ ዕጩ ሆነው በመመረጥ፤ 40 ዓመት ገደማ የቆዩበት ስልጣን ማስቀጠል የሚችሉበትን መንገድ ጠረጉ።
ፕሬዝዳንት ሙሰቬኒ እጩ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ለምርጫ እንዲቀርቡ ለተደረገላቸው ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ከተመረጡም የኡጋንዳን ወደ "ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር" እንድትሆን የማድረግ ተልዕኮአቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የሙሴቬኒ ተቺዎች፤ ፕሬዝዳንቱ እ.አ.አ በ1986 የአማጺ ቡድን መሪ ሆነው የሀገሪቱን ሥልጣን ከተቆናጠጡበት ጊዜ አንስቶ ሀገሪቱን በአምባገነንነት ሲገዙ መቆየታቸውን ያነሳሉ።
ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ በተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ አሸንፈዋል።
በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግም ለፕሬዝዳንትነት በሚወዳደሩ እጩዎች ላይ የተቀመጡት የዕድሜ እና የሥልጣን ዘመን ገደቦችን ለማስወገድ ሲባልም የሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሁለት ጊዜ ተሻሽሏል።
በሚቀጥለው ዓመት ጥር በሚካሄደው ምርጫ የሙሴቬኒ ዋና ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ከፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝነት ወደ ፖለቲከኛነት የተለወጠው ቦቢ ዋይን ነው።
ዋይን፤ 'ናሽናል ዩኒቲ ፕላትፎርም' የተሰኘው ፓርቲው በእጩነት እንዲቀርብ የሚመርጠው ከሆነ ከሙሴቬኒ ጋር እንደሚፎካከር በሚያዝያ ወር ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
ነገር ግን እየጨመረ በመጣው የመንግስት አፈና የተነሳ በተቃዋሚነት መንቀሳቀስ "ፈታኝ" እየሆነ መምጣቱን ጠቅሷል።
"ኡጋንዳ ውስጥ ተቃዋሚ ውስጥ መሆን ማለት አሸባሪ ተብሎ መፈረጅ ማለት ነው" ብሏል።
ትክክለኛ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒ የሆነው ዋይን፤ በ2021 በተካሄደው ምርጫ 35 በመቶ ድምጽ በማግኘት የሀገሪቱን 59 በመቶ ባገኙት ሙሴቬኒ ተሸንፏል።
ይሁን እንጂ ምርጫው የተጭበረበረ እና ተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ የተወሰደበት እንደነበር የሚጠቅሱ ውንጀላዎች ይቀርቡበታል።
ሌላኛው ታዋቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኪዛ ቤሲግዬ በሀገር ክህደት ወንጀል በመከሰሱ ከህዳር ወር አንስቶ በእስር ላይ ይገኛል።
ፖለቲከኛው በበኩሉ ውንጀላውን በማጣጣል እስሩ ፖለቲካዊ መሆኑን ይናገራል።
ፕሬዚዳንት ሙሰቬኒ እጩ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው የ 'ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት' ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር በኡጋንዳ መረጋጋት እና እድገት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
"ከዚህ ቀደም አውሮፓ ሲለወጥ እና አፍሪካ ባርነት ውስጥ ሆነ ስትቆረቁዝ ስትሆን እንደነበረው እንዳይሆን" ኡጋንዳ፤ "የታሪክ አውቶቡስ እንዳያመልጣት" ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ሙሰቬኒ አክለውም ኡጋንዳ "ጥራት ያለው መወንጨፍ" እንድታደርግ እና "ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ያለው ሀገር" እንድትሆን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
"እስያ ውስጥ ያነሰ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏቸው ሌሎች ሀገሮች አድርገውታል፤ እኛ ማድረግ እንችላለን" ሲሉ ተደምጠዋል።